ቀጥታ፡

በብሄረሰብ አስተዳደሩ ዘግይቶ የጣለውን ዝናብ በማቀብ ለሰብል ልማት ለማዋል ርብርብ እየተደረገ ነው

ሰቆጣ ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዘግይቶ የጣለውን ዝናብ በማቀብ ለሰብል ልማት ለማዋል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የአስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ገለፀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤  አብዛኛው በአስተዳደሩ ስር ያሉ አካባቢዎች ዝናብ አጠር በመሆናቸው የዝናብ እጥረቱን በመቋቋም ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ይገኛል።

በዚህም 120 ሺህ 638 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን በተደረገ ጥረት እስካሁን 80 በመቶ ያህሉን ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ከተዘራው መሬት ውስጥም 57 ሺህ 612 ሄክታሩ ድርቅን የሚቋቋሙና ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎችን በመለየት ማልማት መቻሉንም አመልክተዋል።

አርሶ አደሩ እስከ አሁን ባከናወናቸው ተግባራትም  ከ9 ሺህ ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ የእርጥበት እቀባ ሥራ ማከናወኑን ተናግረዋል።

ከአካባቢው የአየር ጸባይ መለዋወጥና የዝናብ መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችል ተባይን ለመከላከል ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመዋል።

አርሶ አደሩ የእርጥበት እቀባውን አጠናክሮ እንዲቀጥልና ሰብሉን ከተባይና ከአረም እንዲከላከል የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የጋዝጊብላ ወረዳ 06 ቀበሌ ነዋሪዎቹ አርሶ አደር እምወደው አየለ እና አርሶ አደር ደስታነህ ንጉሡ በበኩላቸው፤ የዝናብ እጥረቱን ለመቋቋም በእርሻቸው ላይ ውሃ የሚያቁሩ ጉድጓዶችን መቆፈራቸውን ተናግረዋል።

ከባለሙያ የሚሰጣቸውን ምክረ-ሐሳብ መሠረት በማድረግ ሰብላቸውን በወቅቱ ዘርተው አሁን ላይ ወደ አረም ሥራ መግባታቸውንም ገልጸዋል።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በ2018/2019 የመኽር እርሻ ወቅት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም