በሰሜን ሸዋ ዞን በማዕድን ሀብት ልማት አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ሸዋ ዞን በማዕድን ሀብት ልማት አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ነው
ደብረ ብርሃን፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦በሰሜን ሸዋ ዞን የማዕድን ሀብትን አልምቶ ጥቅም ላይ በማዋል አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን የዞኑ የማዕድን ሀብት ልማት መምሪያ ገለጸ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ታደሰ በቀለ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የባህላዊ ማዕድናት ምርትና ግብይት ሕጋዊ መስመር ተከትሎ እንዲከናወን ተደርጓል።
በዚህም 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ቶን ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ እንደተቻለ ነው ያመለከቱት።
የኢንዱስትሪ፣ የኮንስትራክሽንና የከበሩ ማዕድናት በጥራት ተመርተው ለገበያ ማቅረብ በመቻሉም ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንደተቻለ ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ በአካባቢው ጂፕሰም፣ ላይምስቶንና ኦፓልን ጨምሮ ከ27 በላይ የከበሩና የኢንዱስትሪ ማዕድናት መኖራቸውን ጥናት ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።
በቀጣይም ዘርፉን በዘመናዊ መንገድ ለመምራትና የግብይት እሴትን ለማጠናከር በጣርማበር ወረዳ የከበሩ ማዕድናት መግዣና መሸጫ የገበያ ማዕከል እየተገነባ ይገኛል ብለዋል።
የአካባቢውን ማህበረሰብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግና የስራ ዕድል ለመፍጠር በግል እና በኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ 247 ባህላዊ ማዕድን አምራች ማህበራት የስራ ፈቃድ መሰጠቱንም አክለው ገልጸዋል።
በእንሳሮ ወረዳ የ"ሽመልስ ማሞ እና ጓደኞቻቸው" ህብረት ሽርክና ማህበር ሰብሳቢ አቶ ሽመልስ ማሞ በበኩላቸው፤ ማህበሩ ለግንባታ አገልግሎት የሚውል ማዕድን አምርቶ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።
ማህበሩ 47 አባላት ያሉት ሲሆን፣ የማዕድን ሀብቱን አምርቶ ከሚገኘው ሽያጭ አባላቱን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በመርሐቤቴ ወረዳ ቁም አምባ ቀበሌ “ሲልካ“ የተባለ ለጠርሙስ ምርት በግብዓትነት የሚያገለግል ማዕድን እሴት ጨምረው በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሆኑ የገለጹት ደግሞ የ"ማክን ትሬዲንግ" ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ደምሴ ናቸው።
ድርጅታቸው አሁን ላይ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ምርታቸውን በተሻለ ፍጥነትና ጥራት ለገበያ ለማቅረብ እየሰሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።