በሐረሪ ክልል የኢንቨስትመንት ፍቃድ እና መሬት ወስደው ወደ ግንባታና ማምረት ባልገቡ 12 ባለሀብቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል የኢንቨስትመንት ፍቃድ እና መሬት ወስደው ወደ ግንባታና ማምረት ባልገቡ 12 ባለሀብቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ
ሐረሪ ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል የኢንቨስትመንት ፍቃድ እና መሬት ወስደው ወደ ግንባታና ማምረት ባልገቡ 12 ባለሀብቶች ላይ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ስረዛና እገዳ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ኢንተርፕራይዝ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ኢንተርፕራይዝ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀምዲ ሰለሃዲን ለኢዜአ እንዳሉት የክልሉ መንግሥት በኢንቨስትመንት ተሰማርተው ለሚገኙና አዳዲስ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ይገኛል።
ከዚህም ባለፈ የባለሀብቶች እንቅስቃሴ ያለበትን ሁኔታ የመስክ ምልከታ በማከናወን በገቡት ውል መሰረት ወደ ስራ ያልገቡ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ባለሀብቱ ከመንግስት የኢንቨስትመንት ፈቃድና መሬት የሚወስደው የክልሉን ልማት ለማፋጠን በመሆኑ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
በዚህም በክልሉ በኢንቨስትመንት አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ መሠረት ቀደም ሲል የኢንቨስትመንት ፈቃድና መሬት ወስደው ወደስራ ያልገቡና ግንባታ ያጓተቱ 3 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰረዙን ተናግረዋል።
እንዲሁም መሬት ወስደው በውሉ መሠረት ወደ ግንባታ ሥራ ባልገቡና የሼድ ግንባታ አጠናቀው ወደ ማምረት ባልገቡ 9 ባለሀብቶች ላይ ደግሞ ፈቃድ የማገድ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የኢንቨስትመንት ፈቃድና መሬት ወስደው አዝጋሚ የግንባታ ሂደት ውስጥ ለሚገኙ 7 ባለሀብቶችም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል ብለዋል።
በባለሀብቶቹ ላይ ከሚወሰደው እርምጃ ጎን ለጎንም ባለሀብቶቹ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች የመፍታት ሥራ ተከናውኗል ሲሉ ተናግረዋል።
በባለሀብቶቹ ላይ እርምጃ መወሰድ መጀመሩም የሌሎች ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራዎች እንዲፋጠኑ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመው በቀጣይም መሰል እርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።
በቀጣይም ባለሀብቶቹ ወደ ሥራ ካልገቡ ፈቃድ በመሰረዝ የወሰዱት መሬት ለመሬት ባንክ ገቢ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 96 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
ለባለሀብቶቹም የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው በማኑፋክቸሪንግ፣ ሆቴል፣ ግብርና፣ በገበያ ማዕከልና በሌሎች ዘርፎች ለመሰማራት ጥያቄ በማቅረባቸው መሆኑን ተናግረዋል።