ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን በሶስት የአፍሪካ ዋንጫዎች የወከሉት ታዋቂው የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ፍስሐ ወልደአማኑኤል ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ከታዩ ታላላቅ ተጫዋቾች አንዱ የሆኑት ፍስሐ ወልደአማኑኤል ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

"ኳስ ፊደሉ" እና "ጠመንጃው" በሚሉ ቅጽል ስሞች የሚታወቁት አቶ ፍስሐ፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጨዋታ ዘመናቸው ከፍተኛ አገልግሎት ሰጥተዋል።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋርም የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና ዋንጫዎችን አሸንፈዋል።

ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይም የብሔራዊ ቡድኑን ማልያ ለብሰው ተሰልፈዋል።

ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ አምርተው ኑሯቸውን እዚያው ያደረጉት አቶ ፍስሐ፣ ለሀገሪቱ ክለቦች ከመጫወታቸው በተጨማሪ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን (ESFNA) መስራች አባል እና ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግለዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በህልፈታቸው የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፣ ለቤተሰብ፣ ለወዳጅ ዘመድ እና ለስፖርት ቤተሰቡ መጽናናትን  ተመኝቷል።        
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም