ቀጥታ፡

ምክክሩ ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ሆና በጠንካራ መሰረት ላይ እንድትገነባ ያስችላል- ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ሆና በጠንካራ መሰረት ላይ እንድትገነባ ያስችላል ሲሉ ተመካካሪዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ዋናው ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በምክክሩ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ እየመከሩ ነው፡፡

ይህ የምክክር ሂደት በኢትዮጵያ ጠንካራ የመግባባት ባህል በመገንባት የበለጸገች ሀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ መሰረት እንደሚጥል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡት ተመካካሪዎች መካከል ጌታቸው ቢነሳው እንዳሉት፣ ኢትዮጵያን ጠንካራ እና ልዩ  የሚያደርጋት ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት፣ በመከባበር እና በመተሳሰብ የሚኖሩባት ድንቅ ሀገር መሆኗ ነው።

ይህ ለዘመናት የቆየው የጸና ሕብረ ብሔራዊነት ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ሆና በጠንካራ መሰረት እንድትገነባ የሚያስችል ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሁላችንም ሀሳቦች በነፃነት ተደምረው የጋራ ሀገራችንን ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ተመካካሪዎች በመገንዘብ ለዘላቂ  ሰላም፣ ዕድገት እና ሀገረመንግስት ግንባታ በንቃት በመሳተፍ ላይ እንገኛለን ብለዋል።



 
ሌላኛዋ ተመካካሪ ወይዘሮ እናና የኋላ፣ እየተካሄደ ያለው የምክክር ጉባኤ በሀገራችን የመጀመሪያው እና ታይቶ የማይታወቅ በመሆኑ የሕዝባችንን አንድነት ይበልጥ የሚያጠናክር ታሪካዊ ጉባኤ መሆኑን ተናግረዋል።

እኛም በምክክሩ ለቀጣይ ትውልድ የሚመጥን ጠንካራ ሀገር ለማስተላለፍ ሀሳባችንን በግልጽነት እና በመከባበር እየሰጠን እንገኛለን ነው ያሉት።

በአሁኑ ሰዓት ለሀገራችን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ሁሉን አቀፍ እና ግልጽ የሆነ ምክክር ብቻ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ አቶ ተስፋዬ አዳነ ናቸው።


 

ይህም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ እና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ጽኑ መሰረት ይጥላል ሲሉ ተናግረዋል።

ተመካካሪዎችም በሰለጠነ አግባብ እና በሰከነ መንፈስ እየተደማመጥን ሀሳባችንን እየገለጽን እንገኛለን ብለዋል።

ቀጣዩ ትውልድ የጸናች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን መረከብ የሚችለው ዛሬ ለሀገራችን በሚበጁ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበን ስንመካከር ብቻ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም