ቀጥታ፡

በምክክር ጉባኤው ምክረ ሀሳቦችን እንዲያጣጥሙ የተዋቀሩት ቡድኖች ዛሬ ከሰዓት ስራቸውን ይጀምራሉ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 7 /2018(ኢዜአ)፦እየተካሄደ በሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ምክረ ሀሳቦችን እንዲያጣጥሙ የተዋቀሩት ስምንት ቡድኖች ዛሬ ከሰዓት ስራቸውን እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ ገለጹ።

በ500 ተሳታፊዎች የተቋቋሙ ቡድኖች በየቡድናቸው ሲመካከሩ ቆይተው ዛሬ አብዛኞቹ ተግባብተው በምክረ ሃሳቦች ላይ ፊርማቸውን በማኖር እየጨረሱ መሆኑንም ተናግረዋል። 

ተመካካሪዎች ተደማምጠው ወደ አንድ የጋራ እና አማካይ ሃሳብ ላይ መድረሳቸውን ጠቁመው፤ በአብዛኞቹ ጉዳዮች ላይ ተስማምተው ስምንቱም ቡድኖች ስራቸውን እያጠናቀቁ ነው ብለዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ ጉባኤ ምክረ ሀሳቦችን እንዲያጣጥሙ የተዋቀሩት ስምንት ቡድኖች ዛሬ ከሰዓት ስራቸውን እንደሚጀምሩም ገልጸዋል።

ቡድኖቹ የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦች ወጥነት ባለው መልኩ እንዲቀርቡ የሚሰሩ መሆናቸውንም ጨምረው አብራርተዋል።

በሂደቱ ቅሬታ የሚያቀርቡ፣ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቡትን ቅሬታዎች ባለን የቅሬታ መፍቻ ስነስርዓት መሰረት ጉዳዩ እየተጠና ውሳኔ የምንሰጥበት ይሆናል ሲሉም አብራርተዋል።  

ሦስት አራተኛው ስራው መጠናቀቁን ያመላከቱት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፤ በሚቀጥለው ምዕራፍ ለረጅም ጊዜ ሲደከምበት የቆየ ምክክር ውጤታማነቱን ለኢትዮጵያ ህዝብ የምናበስርበት ይሆናል ብለዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም