ማዕከሉ ከእንስሳት ሀብት የሚገኘውን የኢኮኖሚ ጥቅም ለማሳደግ ሚናው የጎላ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከሉ ከእንስሳት ሀብት የሚገኘውን የኢኮኖሚ ጥቅም ለማሳደግ ሚናው የጎላ ነው
ጂንካ፣ ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኦሞ ዞን በና ፀማይ ወረዳ የቀይ-አፈር የኤክስፖርት እንስሳት ማሰባሰቢያ ማዕከል መገንባት አርብቶ አደሩና ሀገር ከእንስሳት ሀብት ተገቢውን የኢኮኖሚ ጥቅም እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ።
በበና ፀማይ ወረዳው የተገነባው የቀይ-አፈር የኤክስፖርት እንስሳት ማሰባሰቢያ ማዕከል ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ የአርብቶ አደር አደጋ ሥጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ስዩም መታፈሪያ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ተገንብቶ ለምረቃ የበቃው የቀይ-አፈር የኤክስፖርት እንስሳት ማሰባሰቢያ ማዕከል ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል።
ማዕከሉ በሀገሪቱ ለሚገኙ 13 የኤክስፖርት ቄራዎች የእርድ እንስሳትን ለማቅረብ ታስቦ የተገነባ መሆኑንም ተናግረዋል።
ማዕከሉ የእንስሳት ክሊኒክ፣ መኖ ማከማቻ መጋዘኖችን ጨምሮ እንስሳቱን በክብደት፣ በተክለሰውነትና በዝርያ መለየት የሚያስችሉ ክፍሎችን አካቶ የተገነባ መሆኑንም አንስተዋል።
የማዕከሉ መገንባት እንስሳቱን ያለ ደላላ በቀጥታ ለገበያ በማቅረብ አርብቶ አደሩ ለእንስሳቱ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ያደርጋል ብለዋል።
በተጨማሪም ሀገሪቱ የእንስሳት ኤክስፖርትን በማሻሻል ከእንስሳት ሀብቷ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት።
በማዕከሉ ያለው ክሊኒክም እንስሳቱ ከመሸጣቸው በፊት አስፈላጊው የሕክምና ክትትልና እንክብካቤ በማድረግ ጥራታቸውን ለማስጠበቅ ያግዛል ብለዋል።
የበናፀማይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንስ ጋርሾ በበኩላቸው ማዕከሉ ለአርብቶ አደሩ የተሻለ ተጠቃሚነት ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን ነው የገለጹት።
የአካባቢው አርብቶ አደር በርካታ ከብቶች ቢኖሩትም በህገወጥ ንግድና በገበያ ትስስር ችግር ተገቢውን ጥቅም ሳያገኝ መቆየቱን አስታውሰው፣ የማዕከሉ መገንባት እነዚህን ችግሮች ይፈታል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ቱሬ በበኩላቸው ኤጀንሲው የኤክስፖርት ስታንዳርድን የጠበቁ የቁም እንስሳትን ከገበያ ማዕከላት በማሰባሰብ በሀገሪቱ ለሚገኙ የኤክስፖርት ቄራዎች እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።
የእንስሳት ማሰባሰቢያ ማዕከሉ ወደአገልግሎት መግባት እንስሳት በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ተሻግረው እንዳይሸጡ በማድረግ ህጋዊ የንግድ ሥርዓትን ያጠናክራል ተብሏል።
በተጨማሪም ደረጃቸውን የጠበቁ የኤክስፖርት እንስሳትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሀገርን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ ነው።
በማዕከሉ የምረቃ መርሀግብር ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩን (ዶ/ር) ጨምሮ የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ እና፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።