ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው በተያዘለት እቅድ መሰረት በስኬት እየተካሄደ ነው-ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 7 /2018(ኢዜአ)፦ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው በተያዘለት እቅድ መሰረት በስኬት በመካሄድ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ሥላሴ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ሥላሴ ፣የምክክር ጉባኤውን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም በአሁኑ ሰዓት የ500 አባላት ስብስብ በየቡድናቸው ሲመካከሩባቸው በቆዩ አጀንዳዎች ላይ ከመግባባት በመድረስ በምክረ ሀሳቦች ላይ ፊርማቸውን አውለው እየጨረሱ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ የሃሳብ አለመግባባቶችና ግጭቶች አልነበሩም ማለት አይደለም ያሉት ኮሚሽነሯ፤ በሃሳቦች ላይ የሚደረጉ ክርክሮች በመኖራቸውም ምክክሩ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አረጋግጠንበታል ብለዋል።

በብዙዎቹ ሀሳቦች ላይ በመደማመጥ ወደ ጋራ ሀሳብ መድረሳቸውን ጠቁመው፥ አሁን ስምንቱም ቡድኖች በበርካታ ጉዳዮች ላይ በመስማማት ስራቸውን እያጠናቀቁ መሆኑን አመልክተዋል።

በቀጣይም እነዚህ ስምንት ቡድኖች የተግባቡባቸውን ምክረ ሀሳቦች የሚያጣጥም (harmonize) የሚያደርግ ቡድን መቋቋሙን ገልጸዋል።

ይህ ቡድን ስራውን ዛሬ ከሰዓት የሚጀመር መሆኑንም ነው የገለፁት።

ይህ የተቋቋመው ቡድን የሚሰራው ስራ አጠቃላይ ለሚቀርበው ምክር ሀሳብ ወጥነት እንዲኖር የሚያስችል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም