ቀጥታ፡

የመረጃ ነጻነት አዋጅ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ትልቅ አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦የመረጃ ነጻነት አዋጅ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ትልቅ አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራው አንደሞ ገለጹ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሚዲያ ሬጉላቶሪ ስርዓትን ማጠናከር የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተፈራርሟል።


 

በመርሀ ግብሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች ታድመዋል።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ ከተቋማቱ የስራ ሃላፊዎች ጋር ተፈራርመዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራው አንደሞ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ባለፉት የለውጥ አመታት የተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

የሀገረ መንግስት ግንባታውም ስሁት እይታን በሚያርም መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው ይህንንም ያለመገናኛ ብዙኃን ተሳትፎ ማሳካት እንደማይቻል ጠቁመዋል።

ለመገናኛ ብዙኃን የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ቁጥራቸውም በጉልህ መጨመሩን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል የዲጂታል ስርዓት የራሱ መልካም እድል ቢኖረውም ጉልህ ተግዳሮቶችን እየፈጠረ መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ትልልቅ ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንን መመከት የሚያስችለውን አቅም ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ስምምነቱ በተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሰራርን የሚያጎለብት መሆኑን ጠቁመው የመረጃ ነጻነት አዋጅ የመረጃ ውስንነትን በጉልህ እንደሚፈታና ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችም ትልቅ አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

በቀጣይም መገናኛ ብዙኃን ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ሚናቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም