ስንዴን በኩታገጠም በማልማታችን ምርታማነታችንን እያሳደግን ነው - ኢዜአ አማርኛ
ስንዴን በኩታገጠም በማልማታችን ምርታማነታችንን እያሳደግን ነው
ሸገር፤ ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፡- በሸገር ከተማ የኩራ ጂዳ ክፍለ ከተማ አርሶ አደሮች በዘመናዊ መንገድና በኩታገጠም የስንዴ ልማት ምርታማነታቸው መጨመሩን ገለጹ።
በኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራስን ለመቻልና ሀገራዊ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተቀየሰው ስትራቴጂ መሠረት፣ በኦሮሚያ ክልልና በሸገር ከተማ አስተዳደር የስንዴ ልማትን በስፋት የማስፋፋት ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
በተለይም በሸገር ከተማ ኩራ ጂዳ ክፍለ ከተማ የሚገኙ አርሶ አደሮች ቀደም ሲል ይጠቀሙበት የነበረውን ባህላዊና አነስተኛ ይዞታን መሠረት ያደረገ የአመራረት ዘዴ በመተው፣ አቅማቸውን አዋህደው በኩታገጠም በማልማት ላይ ይገኛሉ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አርሶ አደሮቹ የስንዴ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከግብርና ሙያተኞች ያገኙትን ግንዛቤና ድጋፍ በመጠቀም ስኬታማ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ።
ከአርሶ አደሮቹ መካከል ወጣት ደቡ ሱልጣን እንደተናገረው፤ ባለፉት ዓመታት የግብርና ሥራችን ያልዘመነና ከፍተኛ ድካም የነበረበት ነው ይላል።
በአሁኑ ወቅት ግን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የኩታገጠም ግብርና መካሄዱ ከፍተኛ ውጤት እያስገኘልን ነው ብሏል።
አርሶ አደር ቡርኩ ታደሰ በበኩላቸው፤ ለዚህ ዓመት የግብርና ሥራ የሚያስፈልጉ ግብአቶች በወቅቱ በመቅረባቸው፣ በበለጠ ተግተን በልማት ሥራችን ላይ ተሰማርተናል ብለዋል።
አርሶ አደሩ በአካባቢያችን በኩታ ገጠም በመደራጀትና ያሉንን አቅሞች በማቀናጀት በልማቱ መሰማራታችን ቀድሞ ከምናገኘው ምርት የበለጠ በማግኘት ተጠቃሚ ሆነናል ብለዋል።
ሌላኛው አርሶ አደር ወጣት ተስፋዬ በቀለ አክሎ እንደገለጸው፤ የኩታ ገጠም ልማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁሞ፣ ይህም አርሶ አደሩ ሕይወቱን ከመቀየር ባሻገር ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ለከተማዋ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ነው ብሏል።
በልማቱ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑና የግብርና ግብአቶችንም በወቅቱ ማግኘታቸው ለሥራቸው ትልቅ መነሳሳት እንደሆናቸው ተናግረዋል።
በሸገር ከተማ የስንዴ ልማትን ማጠናከር የአርሶ አደሮችን ሕይወት ከመቀየር ጎን ለጎን፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የከተማዋን ኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠን ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማዋ የግብርና እና ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ ግርማ ሀይሉ መግለጻቸው ይታወሳል።
በከተማዋ ኩራ ጂዳ ክፍለ ከተማ በ340 ሄክታር መሬት ላይ በኩታገጠም አሰራር ለምርጥ የስንዴ ዘር ብዜት የሚሆን የዘር መዝራት ስራ ትናንት ተከናውኗል።