ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከመስህብ ስፍራ ጎብኝዎች ሁለት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ተገኘ

ሳጃ፤ ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፈው በጀት ዓመት ከ967 ሺህ በላይ የመስህብ  ስፍራ ጎብኚዎች ሁለት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ መገኘቱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

“የባህልና ቱሪዝም እመርታ ለክልላችን ሁለንተናዊ ከፍታ” በሚል መሪ ሐሳብ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም እና የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ እቅድ  ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በሳጃ ከተማ እየተካሄደ ነው።

​በመድረኩም የቢሮው ኃላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ እንደገለፁት፤ በ2018 በጀት ዓመት ​በክልሉ የሚገኙ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ መስህብ ስፍራዎችን የማልማት፣ የማስተዋወቅና ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ስራዎች በስፋት ተከናውነዋል፡፡ 


 

ይህም በበጀት ዓመቱ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ምክንያት ከመሆን ባሻገር ለክልሉ ኢኮኖሚ ተጨማሪ አቅም መፍጠር ማስቻሉን ጠቁመው ከ967 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች የመስህብ ስፍራዎችን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል።

ከጎብኚዎቹ ውስጥ 17 ሺህ 500 የውጪ ጎብኚዎች መሆናቸውን ገልጸው ከዚህም ከ1 ቢሊዮን 850 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልፀዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን የማልማት ተግባር በተጠናከረ ሁኔታ መከናወኑን ተናግረው የጢያ አለም አቀፍ ቅርስን ጨምሮ 5 የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች በ6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በክልሉ ከ295 በላይ መዳረሻ ስፍራዎች መኖራቸውን ጠቁመው 1 ሺህ 805 የመስህብ ዓይነቶችን በመለየትና በማደራጀት የመስህብ ስፍራ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የየም ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ዝናብ በበኩላቸው በዞኑ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመለየት፣ በማልማት እና በማስተዋወቅ የዞኑን መልካም ገፅታ ከመገንባት ባሻገር ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ የማሳደግ ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በዞኑ በየዓመቱ ጥቅምት 17 የሚከናወነው ባህላዊ የመድኃኒት ለቀማ ''ሳሞኤታ'' የህዝቡን ሃገር በቀል እውቀት አጉልቶ በማሳየት  ለዞኑ የቱሪዝም ዕድገት ትልቅ ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩም የክልሉ፣ የዞንና የልዩ ወረዳ አመራሮች እና የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም