በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አምስት ዓመታት ከ96 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል -አቶ አወሉ አብዲ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አምስት ዓመታት ከ96 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል -አቶ አወሉ አብዲ
ጅማ፤ ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል የሕዝቡን እርካታ የሚያረጋግጡና የአገልግሎት አሰጣጡን የሚያዘምኑ ዘመናዊ ተቋማትን የመገንባትና የማደራጀት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲ ተናገሩ።
በኢትዮጵያ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር፣ የቢሮክራሲና የዘመናዊ አሰራር እጥረት ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ሀገራዊ የሪፎርም ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
በዚህም መሠረት በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሕዝቡን እርካታ የሚያረጋግጡ፣ አሰራርን ግልጽና ቀልጣፋ የሚያደርጉ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን መሠረት ያደረጉ ተቋማዊ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።
ይህ የአገልግሎት አሰጣጥን የማዘመንና ዘመናዊ ተቋማትን የመገንባት እንቅስቃሴም የቢሮክራሲ እንግልትንና ሙስናን በመቀነስ፤ አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ፣ ዘመናዊ የአገልግሎት ማዕከላትን በመገንባትና የመንግሥት መዋቅርንና የሰው ኃይል አቅምን በማሳደግ ረገድ ውጤቶች እንዲመዘገቡ አስችለዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ የሚከናወኑት እነዚህ የቴክኖሎጂና የተቋማት ግንባታ ሥራዎች የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ከመመለሳቸው ባሻገር፣ ለክልሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መፋጠን ምቹ ሁኔታን እየፈጠሩ ይገኛሉ።
በዛሬው ዕለትም የዚሁ ጥረት አካል የሆነው እና ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የጅማ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ህንፃ ተመርቋል።
በምረቃው ላይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝደንት አወሉ አብዲ፣ በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ነመራ ቡሊ እና የተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
አቶ አወሉ አብዲ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች ከ96ሺህ በላይ የልማት ፕሮጀክቶች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹም የህብረተሰቡን ጥያቄ ባማከለ መልኩ የተገነቡ መሆናቸውንም አክለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ 96 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ተገንብተው የተቀላጠፈ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ነው ያሉት።
"ወደፊትም ለህዝባችን የገባነውን ቃል በተግባር የመወጣት ሀላፊነታችንን ለማሳካት በትጋት እንሰራለን" ብለዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ በመደመር እሳቤ የተተገበሩ ተግባራት በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚው ዘርፎች ትልቅ ለውጥ አምጥተዋል ብለዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ ነመራ ቡሊ በበኩላቸው፤ ብልፅግና ፓርቲ በክልሉ ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት እና ትምህርትና ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት እንዲሁም ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት ያደረጋቸው ጥረቶች ውጤታማ ናቸው ብለዋል።
ባለፉት ስድስት እና ሰባት ዓመታት በክልሉ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እድገት መመዝገቡንም ለአብነት አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ምርታማነትን በማሳደግ እና የስራ ዕድልን በማስፋት ረገድ ፓርቲው ለህዝብ የገባውን ቃል እየተወጣ መሆኑን አክለዋል።
ዛሬ የተመረቀው የአስተዳደር ህንፃ 125 ክፍሎች ያሉት እና 17 የመንግስት ሴክተሮች አገልግሎት የሚሰጡበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቲጃኒ ናስር ናቸው።