በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያስተናግዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያስተናግዳሉ
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያስተናግዱ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ በስፋት ያስተናግዳሉ።
በደቡብ ምዕራብ፤ ምዕራብ፤ ሰሜን ምዕራብ፤ ሰሜን፤ መካከለኛው፤ ምሥራቅ እና ሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚኖራቸው በመግለጫው ተመላክቷል።
በምዕራብ፤ ሰሜን ምዕራብ ፤ ደቡብ ምዕራብ እና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች እርጥበታማ የአየር ሁኔታም ከመጠናከሩ ጋር በተገናኘ በተጠቀሱት አካባቢዎች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያስተናግዱ ይጠበቃል።
በሰሜን ምሥራቅ፤ ምሥራቅ እና ደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በሰሜን ምዕራብ፤ ደቡብ ምዕራብ፤ መካከለኛው፤ ምዕራብ እና ሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱን አካባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ ከሚከሰቱት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ጋር ተያይዞ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖርም ኢንስቲትዩቱ ጠቁሟል።
ኢንስቲትዩቱ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ፤ የመኸር ሰብል አብቃይ፤ አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረውን እርጥበት ለግብርና ስራዎቻቸው ውጤታማነት በአግባቡ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርቧል።
በዚህም መሰረት የአጭር ጊዜ የመኸር ሰብሎችን በመዝራት ፣የሰብል በሽታንና አረምን አስቀድሞ በመከላከል ፣ተዳፋታማ ማሳዎች ላይ የተዘጉ የማፋሰሻና የማንጣፈፊያ ቦዮችን በማስተካከል የእርጥበት ሁኔታዎን ወደ ውጤት ሊያውሉ እንደሚገባ አመላክቷል።
በተጨማሪም እርጥበት አጠር አካባቢዎች የዝናብ ውሀን ማሰባሰብና ማጠራቀም፣ የመሬት መንሸራተትና የአፈር መሸርሸር መከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን፤ የማዳበሪያ አጠቃቀምን በትክክለኛው ሰዓት ጠቀም ተገቢ መሆኑንም ገልጿል።
ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት የሚያስተናግዱ አካባቢዎችም የሚገኘውን እርጥበት ለእርሻ በቂ መሆኑን በማረጋገጥ የአጭር ጊዜ የመኸር ሰብሎችን መዝራት ፣የአፈር ውስጥ የትነት መጠንን ለመቀነስ የሚያስችሉ አሰራሮችን መዘርጋት እና ለእንስሳት የግጦሽ ሳርን በአግባቡ መጠበቅና ማዘጋጀት ሊወሰዱአቸው ከሚገቡ ጥንቃቄዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸው ተጠቁሟል።
በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላቶች የእርጥበት ሁኔታው በውሀ አካላት ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ በመገንዘብ የጎርፍ አደጋ የመሬት መንሸራተት እንዲሁም የደራሽ ወንዝ ሙላት እና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎችን መከላከል የሚስችሉ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል።