መገናኛ ብዙሃን ብሔራዊ ጥቅምን የስራዎቻቸው ማዕከል ሊያደርጉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን ብሔራዊ ጥቅምን የስራዎቻቸው ማዕከል ሊያደርጉ ይገባል
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና የህዝብ ሰላምን የስራዎቻቸው ማዕከል ሊያደርጉ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን የሚዲያ ሬጉላቶሪ ሥርዓትን ማጠናከር የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ ከተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተፈራርመዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ በዚሁ ወቅት፤ መገናኛ ብዙሀን ለሀገር እና ትውልድ ግንባታ የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።
ዘመኑ ሀሰተኛ መረጃ በስፋት የሚስተዋልበት ጋዜጠኝነትና አክቲቪዝም የተደበላለቁበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ሀገር እና ትውልድን የሚገነባው ትልቁ መሳሪያ ለግጭት እየዋለ እንደሚገኝ አንስተው፤ ይህም የዲጂታል ሚዲያ የቁጥጥር አቅምን የሚፈትን መሆኑን ገልጸዋል።
የዲጂታል ሚዲያውን አሉታዊ ተጽዕኖ መቆጣጠር የሚያስችል ፖሊሲ እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት።
ብሔራዊ ጥቅም እና የህዝብ ሰላም እና ደህንነት የመገናኛ ብዙሃን የስራዎቻቸው ማጠንጠኛ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ለዚህም ስርዓት መፍጠር እና ተሞክሮዎችን መውሰድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የመረጃ ነጻነት አዋጅ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ ሁኔታ መዘጋጀቱን የገለጹት አቶ እውነቴ አለነ፤ተቋማት መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙሀን ክፍት የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
ለሀገር ሰላም እና እድገት የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አንስተው፤ መገናኛ ብዙሀን ይህንን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ይገባቸዋል ብለዋል።