ስምምነቱ የመገናኛ ብዙሀን የቁጥጥር እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ መምራት የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
ስምምነቱ የመገናኛ ብዙሀን የቁጥጥር እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ መምራት የሚያስችል ነው
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ከተለያዩ ተቋማት ጋር ያደረገው ስምምነት የመገናኛ ብዙሀን የቁጥጥር እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ መምራት የሚያስችል መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን የሚዲያ ሬጉላቶሪ ሥርዓትን ማጠናከር የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተፈራርሟል።
በመርሀግብሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት የሥራ ሀላፊዎች ታድመዋል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ ከተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተፈራርመዋል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ስምምነቱ የመገናኛ ብዙሀን ቁጥጥር እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በማስተሳሰር ቅንጅታዊ አሰራር ለመዘርጋት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
በተቋማት መካከል ፈጣን እና ዲጂታል የመረጃ ልውውጥ ስርዓትን በመዘርጋት ክፍተትን የሚያስወግድ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመገናኛ ብዙሀን የቁጥጥር እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በጋራ እና በተቀናጀ መልኩ መምራት የሚያስችል አሰራር እንደሚፈጥርም ነው የተናገሩት።
እንዲሁም በሚዲያው ዘርፍ የህግ ማስፈጸም ስራዎችን በጥራት እና በብቃት በማከናወን ህጋዊነት፣የህዝብ ደህንነትና ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።
የዘርፉን ተለዋዋጭ ሁኔታ ያገናዘበ ፖሊሲ፣ህግና አሰራርን የሚዘረጋ መሆኑንም ጠቁመዋል።