በምክክሩ ኢትዮጵያን የሚያሻግሩ ገንቢ ሀሳቦች እየተነሱ ነው-ተመካካሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በምክክሩ ኢትዮጵያን የሚያሻግሩ ገንቢ ሀሳቦች እየተነሱ ነው-ተመካካሪዎች
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያን የሚያሻግሩ ጠንካራ እና ገንቢ ሀሳቦችን በማንሳት ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውን ተመካካሪዎች ገለጹ።
ዋናው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ነው።
በምክክሩ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ እየመከሩ ይገኛሉ።
ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የምክክር ጉባኤ ለዘመናት የዘለቁ አለመግባባቶችን በምክክር በመፍታት ለዘላቂ ሰላም እና ጠንካራ ሀገር ግንባታ መሰረት እንደሚጥል ተመካካሪዎች ለኢዜአ ገልጸዋል።
በዚህ ሂደት ታሪካዊ እና ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን በመወጣት ኢትዮጵያን የሚያሻግር ገንቢ ሀሳብ በነጻነት በማንሳት የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ከተመካካሪዎች መካከል አርሶ አደሮችን በመወከል እየተሳተፉ የሚገኙት ተመካካሪ አዳነ ዮሐንስ፣በሀገራዊ ምክክሩ በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ በመከባበር እና በመደማመጥ እየተመካከርን እንገኛለን ብለዋል።
ይህ የምክክር ሂደት እጅግ ስልጡን በመሆኑ ለጋራ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሔ በማበጀት ኢትዮጵያዊ የወንድማማችነት እሴትን ይበልጥ እንደሚያጎለብት ተናግረዋል።
ተመካካሪዎችም ኢትዮጵያን የሚያሻግር ጠንካራ እና ገንቢ ሀሳቦችን በማንሳት ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ ናቸው ብለዋል።
ይህም ለቀጣይ ትውልድ የምትመች ጠንካራ ሀገር ለማስረከብ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽንን በመወከል በምክክሩ እየተሳተፉ የሚገኙት ተመካካሪ ጉርሜሳ ሌንጮ በበኩላቸው፣ የምክክር ጉባኤው ቀደም ሲል ለአለመግባባት ምክንያት ሆነው የቆዩ ጉዳዮችን በመለየት በጉዳዮቹ ላይ ተመካክረን የጋራ መግባባት ላይ እንድንደርስ የሚያስችል ታሪካዊ ጉባኤ ነው ብለዋል።
በምክክሩ ሀሳባችንን በነፃነት እያንጸባረቅን እንገኛለን ያሉ ሲሆን፣ ተቀራርቦ መመካከር ለዘላቂ ሰላም እና ለጠንካራ ሀገር ግንባታ እጅግ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
ተመካካሪ ታዬ ሎዮ በበኩላቸው፣ የምክክር ሂደቱ እጅግ አሳታፊ እና ሁሉም ሀሳቡን በነፃነት የሚገልጽበት አካታች ጉባኤ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲህ ያሉ ምክክሮች እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በመነጋገር ውስጥ የሚመጣው ቅርርብ የሀገር ግንባታ ሂደት ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው አብራርተዋል።
ምክክሩ ለዘመናት ለዘለቁ ችግሮች የጋራ የሆነ መፍትሔ በማበጀት ኢትዮጵያን ለትውልድ እንደሚያሻግር ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።