በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በመኸር እርሻ ከ500 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በመኸር እርሻ ከ500 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል
ጎንደር፤ ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በመኸር እርሻ ከ500 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና በመምሪያ ገለጸ።
በዞኑ በ2018/2019 የምርት ዘመን ከ586 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን ምርታማነትን ለማሳደግ ግብ
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ንጉሤ ማለደ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ የተሻሻሉ አሠራሮችና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም 501 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል።
በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ በቆሎ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ጤፍና ሰሊጥ እንዲሁም ሌሎች የሰብል ዘሮች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
በምርት ዘመኑ የመካናይዜሽን እርሻን በማስፋፋት በትራክተር ለማረስ ከታቀደው ከ71 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ እስካሁን 94 በመቶውን ማሳካት መቻሉንም ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በምርት ዘመኑ ለማልማት ከታቀደው መሬት ከ24 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ለምርት ዘመኑ ከቀረበው ከ627 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 403 ሺህ ኩንታሉ ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ መዋሉን አመልክተዋል።
ዝናብ ዘግይቶ መጣል በጀመረባቸው አካባቢዎች የተገኝውን እርጥበትን በመጠቀም በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎችን አርሶ አደሩ ለይቶ እንዲያለማ ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
በዞኑ ጠገዴ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ሽባባው መሪድ በበኩላቸው፤ የመካናይዜሽን እርሻን በመጠቀም ከ500 ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈናቸውን ተናግረዋል።
መሬቱን ያለሙት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው አኩሪ አተር፣ ጥጥ፣ ሰሊጥና ማሽላ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስከ 8 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎችም ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።
የሰው ጉልበትን በዘመናዊ የእርሻ ትራክተር በመተካት የሰብል ምርታማነታቸውን ማሳደጋቸውን የገለጹት ደግሞ በዚሁ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ቸሬ ገብሬ ናቸው።
የተረከቡትን 77 ሄክታር መሬት ቀድመው በማለስለስ በጥጥና በአኩሪ አተር ሰብሎች ሸፍነው እያለሙ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በዞኑ በ2017/2018 የምርት ዘመን ከለማው 552 ሺህ 895 ሄክታር መሬት 18 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።