ቀጥታ፡

የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ላሞች በይርጋዓለም ከተማ የወተት አልሚዎችን ተጠቃሚነት አሳድገዋል

‎ይርጋለም፤ ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፡-የተሻሻለ ዝርያ ካላቸው ላሞች በሚያገኙት የወተት ምርት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ማደጉን በወተት ልማት ዘርፍ የተሰማሩ የይርጋዓለም ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ በበኩሉ በክልሉ በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት በመከናወናቸው አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጿል፡፡

በማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ይርጋዓለም ከተማ በወተት ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የተሻሻለ ዝርያ ካላቸው ላሞች የሚያገኙት የወተት ምርት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን አሳድጎታል።

ከተጠቃሚዎቹ መካከል አቶ ደሳለኝ ጥላሁን የወተት ልማት ሥራቸውን የተሻሻለ ዝርያ ባላቸው አነስተኛ የወተት ላሞች እንደጀመሩ ገልጸዋል።

በሂደት ሥራቸውን በማስፋፋት በአሁኑ ወቅት የላሞችና ጊደሮቻቸውን ቁጥር ከ30 በላይ ለማድረስ እንደቻሉ ገልጸው፣ በዘርፉ ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራ ትርፋማ መሆን ይቻላል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በቀን ከ500 ሊትር በላይ የወተት ምርት እንደሚያገኙ ገልፀው፣ ከሌሎች ጋር በማህበር ተደራጅተው የወተት ምርቶቻቸውን ለኢንዱስትሪዎችና ለአካባቢው ማህበረሰብ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግስት የከብቶቻቸውን ጤና ከመጠበቅ ጀምሮ ውጤታማ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረገላቸው መሆኑንም አመልክተዋል።

ሌላኛው ነዋሪ አቶ ደረጀ ኤጃሞ ሥራውን የተሻሻለ ዝርያ ባለት አንድ የወተት ላም እንደሆነ ተናግረው ከመንግስት የተመቻቸላቸውን የብድርና የቦታ ድጋፍ ተጠቅመው ጠንክረው በመስራታቸው ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የላምና የጊደሮችን ቁጥር 36 ማድረሳቸውን ጠቅሰው፣ እንስሳቶቻቸውን በበቂ ሁኔታ ለመመገብ ከሁለት ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተለያዩ የእንስሳት መኖ ሣሮችን ተክለው እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በየቀኑ የሚያገኙትን ከ200 ሊትር በላይ ወተት ለከተማው ማህበረሰብ በማቅረብ ገቢያቸውን እያሳደጉና ሀብት እያፈሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ 

የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ምክትልና የዝርያ ማሻሻልና መኖ ልምት ዘርፍ ኃላፊ አደገ አለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልሉ ከአዘርፉ የአርሶ አደሩንና የግል አልሚዎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሲሰራ ቆይቷል። 

በተለይ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣ በመኖ አቅርቦት እና ጤና አጠባበቅ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

የዝርያ ማሻሻል ሥራው በአምስት ዓመት ውስጥ ከአምስት እጥፍ በላይ ማደጉን ገልጸው፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 250 ሺህ የዳልጋ ከብቶችን ዝርያ ማሻሻል እንደተቻለ ገልጸዋል።


 

በመኖ አቅርቦትና በእንስሳት ጤና አጠባበቅ ሥራም እንዲሁ ከፍተኛ ውጤት እንደተገኘ ያነሱት አደገ (ዶ/ር)፣ እነዚህ ተግባራት በወተት ምርትና ምርታማነት ላይ እመርታ ማምጣታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ 

ቀደም ሲል በአካባቢው ሲመረት የነበረው ወተት ቤት ፍጆታ እንደማያልፍ አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ከአካባቢው አልፎ ለኢንዱስትሪዎች ማቅረብ የተቻለበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ብለዋል። 

ለዚሀም ባለፈው በጀት ዓመት ከተመረተው 728 ሚሊዮን ሊትር ወተት 30 በመቶ የሚሆነውን ለኢንዱስትሪዎች መቅረቡን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በተያዘው የ2019 በጀት ዓመትም ከ889 ሚሊዮን ሊትር በላይ ወተት ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም