በድሬዳዋ ወደ ማምረት በተሸጋገሩ አዳዲስ አምራች ኢንዱስትሪዎች በተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ ሆነናል-ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ ወደ ማምረት በተሸጋገሩ አዳዲስ አምራች ኢንዱስትሪዎች በተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ ሆነናል-ወጣቶች
ድሬደዋ፣ ነሐሴ 7/2018(ኢዜአ) በድሬዳዋ በ''ኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ ወደ ማምረት በተሸጋገሩ አዳዲስ አምራች ኢንዱስትሪዎች በተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ወጣቶች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚታዩ የአሰራር ማነቆዎችን በመፍታት የአገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማሳደግ ዘመናዊ እና ውጤታማ ምህዳር መፍጠር አስችሏል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ንቅናቄው አምራቾች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ለማስቻል፣ የኃይል፣ የፋይናንስ፣ የመሬት እና የግብዓት አቅርቦት ጥያቄያቸውን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ፈጣን ምላሽ እንዲያገኝ አድርጓል።
ይህም በርካታ አዳዲስና ነባር ፋብሪካዎች ግንባታቸውንና ማስፋፊያቸውን በፍጥነት አጠናቀው ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ ያስቻለ ሲሆን፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን ማዳን አስችሏል።
እንዲሁም ለበርካታ ዜጎች፣ በተለይም ለወጣቶች፣ ቋሚና አስተማማኝ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦን አበርክቷል።
አስተየየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶችም፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ድጋፍ እና ክትትል ወደ ማምረት በገቡ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች በተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው የዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች መካከል ወጣት አሸናፊ አስናቀ እና ወጣት ዱርሲቱ ሁሴን፤ በተፈጠረላቸው የስራ ዕድል ተጠቅመው ህይወታቸውን እየለወጡና ተጨማሪ ትምህርት እየተማሩ መሆኑን አንስተዋል።
በኡርጂ ሳሙና ፋብሪካ በማሽን ኦፕሬተርነት ተቀጥረው የተሻለ ገቢ ማግኘት እንደቻሉ የተናገሩት ደግሞ ወጣት ኤሊያስ ሐሰን እና ወጣት ኢብሳ አሊ ናቸው።
የፋብሪካ ባለቤቶችና የስራ አመራሮች በበኩላቸው ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅም ወደ ምርት ሲገቡ ተጨማሪ የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩም ገልጸዋል።
የአሜን የካርቶን ፋብሪካ ባለቤት አቶ ብሩክ በቀለ በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩ ባደረገላቸው ድጋፍ በ62 ሚሊዮን ብር ካፒታል በአንድ ዓመት ግንባታ አጠናቀው ማምረት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
የፋብሪካው ወደ ስራ መግባት ለ27 ሰዎች ቋሚ የስራ ዕድል በመፍጠሩና ከውጭ የሚገባን ምርት ማስቀረቱን ጠቁመዋል።
የፋብሪካው ምርት ጥራቱን የጠበቀ ከመሆኑም በላይ ከፕላስቲክ የጸዳች ድሬዳዋን ለመፍጠር የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኡርጂ ሳሙና ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሐምዲያ ዑመር በበኩላቸው የድሬዳዋ አስተዳደር ለፕሮጀክት ማስፋፊያ መሬት፣ ለፋይናንስ እና ለኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ጥያቄቸው ፈጣን ምላሽ እንደሰጣቸው ተናግረዋል።
ይህም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ማስቻሉን ገልጸው ለ46 ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውንም አስረድተዋል።
የተለያዩ የውሃ ማጠራቀሚያ (ሮቶ) ምርቶቹን ወደ ጅቡቲ እና ሀርጌሳ ከተሞች በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ያለው አሽራፍ የፕላስቲክ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ንጉሴ ፋብሪካው ለ40 ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
አስተዳደሩ ለማምረቻ ቦታ ጥያቄያቸው ፈጣን ምላሽ በመስጠቱ በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት እንደተነሳሱም ገልጸዋል።