የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ከ559 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ከ559 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ
ባህር ዳር ፤ነሐሴ7/2018 (ኢዜአ)፡- ከአማራ ክልል የቅባትና ጥራጥሬ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ559 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የሰብልና የኢንዱስትሪ ምርቶች ግብይት ዳይሬክተር አቶ ልንገረው አበሻ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ወደ ውጭ ተልከዋል።
ወደ ተለያዩ ሀገራት ከተላኩት የግብርና ምርቶች ውስጥ ከ1 ሚሊዮን 942 ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥና ኑግ እንደሚገኙበት የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ቀሪው ደግሞ የቦሎቄ፣ የአኩሪ አተር፣ የማሾና የቡና ምርቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።
በበጀት ዓመቱ ወደ ውጭ ከተላኩ የቅባት፣ የጥራጥሬና የቡና ምርቶች በአጠቃላይ ከ559 ሚሊዮን 880 ሺህ 84 የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ተናግረዋል።
ምርቶቹ ከተላኩባቸው ዋና ዋና አካባቢዎች መካከል አውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ ህንድ፣ ሩቅ ምስራቅ እና የእስያ ሀገራት እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
በአዲሱ የበጀት ዓመትም የተሻለ ምርት በጥራትና በብዛት አምርቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በ2016/2017 የበጀት ዓመት ከክልሉ ከ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የቅባትና የጥራጥሬ ምርቶች ወደ ተለያዩ ሀገራት መላካቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።