የኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ እመርታ የተረጂነት አስተሳሰብን በመስበር ወደ አዲስ ታሪካዊ የምርታማነት ምዕራፍ እያሸጋገረ ነው - አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ እመርታ የተረጂነት አስተሳሰብን በመስበር ወደ አዲስ ታሪካዊ የምርታማነት ምዕራፍ እያሸጋገረ ነው - አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ እመርታ የተረጂነት አስተሳሰብን በመስበር ሀገሪቱን ወደ አዲስ ታሪካዊ የምርታማነት ምዕራፍ እያሸጋገራት መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል አቅርቦት በራሳቸው አቅም መሸፈን መጀመራቸውንም አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ የሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን ቀድሞ በመከላከልና አደጋ ሲደርስ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል የአሰራርና የሕግ ማሻሻያ ተደርጓል።
ይህም ዜጎችን ከተረጂነት አመለካከት በማላቀቅ የአደጋ ተጋላጭነትንና የሰብዓዊ ድጋፍ ተጠቃሚዎችን ቁጥር በመሠረታዊነት መቀነስ በማስቻል እመርታዊ ውጤት እያስገኘ ነው።
ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን ተነሳሽነት የተረጅነት አስተሳስብን ሰብሯል።
በዓለም አቀፍ አጋር አካላት ላይ የተመረኮዘውንና ዋስትና የማይሰጠውን የሰብዓዊ ድጋፍ ምላሽ በራስ አቅም በመሸፈን የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትልቅ የታሪክ ለውጥ መፈጠሩን ገልጸዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የአደጋ ስጋት አመራር ፖሊሲ በማውጣት፣ አዋጆችንና መመሪያዎችን በመከለስ ዜጎችን ከተረጂነት ለማላቀቅ በትኩረት መሰራቱንም አስረድተዋል።
ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን ክብር ከማስጠበቅ ባሻገር ነፃነትንና የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሰረት እየጣለ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለዚህም የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ተቋቁሞ ዜጎች የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን አንስተዋል።
የአመለካከት ለውጡና በኢኮኖሚው ዘርፍ የተከናወኑ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸው የአደጋ ተጋላጭነትንና የሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊዎችን ቁጥር ለመቀነስ አስችሏል ብለዋል።
ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን በተደረገው ጥረትም የሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊዎችን ቁጥር በ2013 ዓ.ም ከነበረበት 27 ሚሊዮን በ2018 ዓ.ም ወደ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የማከማቻ መጋዘኖችና የሎጂስቲክስ ሥርዓት ተጠናክሯል ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በቀጣይም የቤተሰብ ኃላፊነትንና የማህበረሰብ አጋርነትን ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የመጠባበቂያ ክምችት ሥርዓት በመዘርጋትና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በማጠናከር ለዜጎች አስተማማኝ ዋስትና እየተፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።
ክልሎችም ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችላቸውን አቅም እያዳበሩ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ስኬት የማንሰራራት ዘመን ብስራት መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እሳት፣ ቅፅበታዊና ሌሎች አደጋዎች ሲያጋጥሙም ከሌሎች ሀገራት ይጠየቅ የነበርን ድጋፍ በመቀነስ የተረጂነት አስተሳሰብን መቀየር እየተቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋን ሰብዓዊ ድጋፍ ምላሽ የመስጠት ሥርዓት ከራስ አልፎ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር የሚተርፍ ልምድ እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።