ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው የተለያዩ ሀሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ በማስቻል ችግሮችን በምክክር ለመፍታት ሰፊ ዕድል ፈጥሯል- ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ በማስቻል፣ ነባር ችግሮችን በምክክር ለመፍታት ሰፊ ዕድል መፍጠሩን ተመካካሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል።

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ናቸው።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመካካሪዎች፤ በምክክሩ እየተነሱ የሚገኙት ሀሳቦች ለዘላቂ የሀገር ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው ብለዋል።

ከተመካካሪዎቹ መካከል የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋምን በመወከል እየተመካከሩ የሚገኙት ተመካካሪ አብዲሳ አበበ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ምክክሩ ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉበትና ሁሉም ሰው ሀሳቡን በነፃነት እያቀረበበት ይገኛል።

ምክክሩ የተለያዩ ሀሳቦች ያለ ገደብ እንዲነሱ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመው፤ ይህም ችግሮችን አሳታፊ በሆነ መንገድ በመመካከር ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገ የሚበጁ መፍትሄዎችን ማምጣት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በተመካካሪዎች እየተነሱ ያሉት ሀሳቦች ኢትዮጵያን ወደ ዘላቂ ሰላም፣ ከፍታና እድገት ለማሻገር እንደሚያግዝ ገልፀው፤ ሂደቱ ለሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።


 

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፓርቲ ተወካይ ስማቸው እንግሶ በበኩላቸው፤በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ ሕዝብ በአንድ ላይ ሲመካከር የመጀመሪያው መሆኑን ገልጸው፤ በምክክሩ እየተነሱ ባሉ ሐሳቦች ላይ በመምከር ወደ አንድ የጋራ መግባቢያ እየተመጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምክክሩ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመው፤ ይህም የተሻለች ሀገርን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊነቷን በማጠናከር ከአፍሪካ አልፋ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዎንታዊ ሚና እንድትጫወት የሚያስችል አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም