በምዕራብ ሸዋ ዞን በመኸር እርሻው ከ916ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ ዞን በመኸር እርሻው ከ916ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል
አምቦ ፤ ነሐሴ 7/2018(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ሸዋ ዞን በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከ916 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ምዕራብ ሸዋ ዞን በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ዋና ዋና እና ምርታማ የግብርና አካባቢዎች አንዱ ነው።
አብዛኛው የዞኑ መሬት ለግብርና ተስማሚ የሆነ ወይናደጋ እና ደጋማ የአየር ጠባይ ያለው ሲሆን፣ አካባቢው በዋናነት በጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ ማሽላ እንዲሁም በጥራጥሬና ቅባት እህሎች አምራችነቱ ይታወቃል።
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ደጀኔ ደቡሼ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በ2018/19 የምርት ዘመን 902 ሺህ 892 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ከእቅድ በላይ 916ሺህ 735 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር ተሸፍኗል።
ከለማው መሬት ከ34 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎም ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የምርት እቅዱን ለማሳካትም ግብዓት መጠቀም፣ ደጋግሞ ማረስ፣ በመስመር መዝራት እና አረምን መከላከል ላይ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረት አብዛኛው ሰብል በኩታ ገጠም የተዘራ እንደሆነ ገልጸው፤ በልማቱ ከ344 ሺህ በላይ አርሶአደሮች ተሳትፈዋል ብለዋል፡፡
የግብርና ባለሙያዎችም አርሶ አደሩ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን እና ሌሎች የተሻሻሉ አሰራሮችን እንዲሁም ግብአትን ተጠቅመው በመዝራት ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም ነው አቶ ደጀኔ የተናገሩት፡፡
በዘር ከተሸፈነው ውስጥ ቀድመው የተዘሩ ሰብሎች አሁን ላይ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በዞኑ የአምቦ ወረዳ አርሶ አደር ሙለታ ጉተማ፤ በመኸር እርሻ ወቅት ተገቢውን ምርት ለማግኘት አንድ ሄክታር ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ በስንዴና በገብስ ሰብል መሸፈናቸውን ተናግረዋል፡፡
በግብርና ባለሙያዎች የሚሰጡ አሰራሮችንና ግብዓቶችን በመጠቀም ጥሩ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
በበጋ መስኖ ያለሙትን ምርት ሙሉ በሙሉ በማንሳት ወደ መኸሩ እርሻ ስራ መግባታቸውን የተናገሩት ደግሞ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር አበራ ቶለሳ ናቸው።
የተፈጥሮ ማዳበሪያንና ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ ተጠቅመው ሁለት ሄክታር መሬት በቆሎ፣ ማሽላ እና ስንዴ ዘር መሸፈናቸውንም ገልጸዋል።
አርሶአደሮቹ በአሁኑ የመኸር እርሻቸውን አከናውነው የመንከባከብ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ።
በዞኑ ባለፈው መኸር ከለማው ከ900 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ 33 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።