ቀጥታ፡

በተለያዩ ሀገራት በኢ-መደበኛ ፍልሰት ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ የነበሩ ዜጎች ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ እየተደረገ ነው - አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2018 (ኢዜአ)፦ በተለያዩ ሀገራት በኢ-መደበኛ ፍልሰት ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ የነበሩ ዜጎች ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።

የሳዑዲ ዓረቢያ ስደት ተመላሽ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ መብትና ክብራቸው ተጠብቆ ወደ ቤተሰቦቻቸው የማቀላቀሉ ሥራ በተቀናጀ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከሳዑዲ ዓረቢያው ንጉሥ ሳልማን የሰብዓዊ እርዳታ ማዕከል ጋር በመተባበር ከስደት ተመላሾችን መልሶ ማቋቋም የሚያስችል የድጋፍ ስምምነት ተፈራርሟል።

በስምምነቱ ወቅትም ከሳዑዲ ዓረቢያው ንጉሥ ሳልማን የሰብዓዊ እርዳታ ማዕከል የተበረከቱ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች የድጋፍ ርክክብ ተካሂዷል።

በዚሁ ወቅት ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ ረጅም ዘመናትን የተሻገረ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው ሀገራት ናቸው።

የሀገራቱ ታሪካዊ ግንኙነትም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የትብብር መስኮች ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት እየተሸጋገረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለአብነትም ከሀገራቱ የንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነት ባሻገር በሕጋዊ የሥራ ስምሪትን በመከተል በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የሙያ መስኮች በሳዑዲ ዓረቢያ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢ-መደበኛ ፍልሰት ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ተጉዘው በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ ትብብር ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የሳዑዲ ዓረቢያው ንጉሥ ሳልማን የሰብዓዊ እርዳታ ማዕከል ከስደት ተመላሽ ዜጎች ሰብዓዊ መብትና ክብራቸው ተጠብቆ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ላበረከተው የቁሳቁስ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በማዕከሉ የተበረከተው የዕለት ደራሽና የማጓጓዣ ቁሳቁስ ድጋፍም የሀገራቱን የረጅም ዘመናት ወዳጅነትና ትብብር የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የሳዑዲ ዓረቢያ አምባሳደር አብዱላህ ሀሰን አልዛህራኒ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያና የሳዑዲ ዓረቢያ ታሪካዊ አጋርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

የተደረገው ድጋፍ ለኢትዮጵያውያን ስደት ተመላሾች ለሚደረገው የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ የሚውል ሲሆን፣ የሁለቱን ሀገራት የረጅም ጊዜ ወዳጅነትና የሰብዓዊ ትብብር እሴት የሚያጎለብት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሳዑዲ ዓረቢያ የኢ-መደበኛ ስደት ተመላሽ ጎራየ ጌትነት፤ በኢ-መደበኛ ስደት ያሳለፉትን አስከፊ ውጣ ውረድ አስታውሷል።

የሳዑዲ ዓረቢያ የኢ-መደበኛ ስደት ተመላሽ ገብረ ሃዋሪያ ሐጎስ፤ ከነበሩበት አስቸጋሪ ሁኔታ ወደ ሀገራቸው በመመለሳቸው የተደረገላቸውን አቀባበልና እንክብካቤ አመስግነዋል።

የሳዑዲ ዓረቢያ የኢ-መደበኛ ስደት ተመላሽ ከማል መሐመድ፤ ያሳለፉትን አስቸጋሪ የሕይወት ውጣ ውረድ በማስታወስ በቀጣይ በሀገሬ ሰርቼ ለመለወጥ እተጋለሁ፤ ኢ-መደበኛ ስደትም አስከፊ ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም