ቀጥታ፡

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አቀፍ የጥናትና ምርምር አገልግሎቶች የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ውጤት እያስገኘ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2018 (ኢዜአ)፦ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አቀፍ የጥናትና ምርምር አገልግሎቶች የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ፕሬዝዳንት ተመስገን ደበሎ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በጋራ መስራት በሚያስችላቸው የትብብር መስኮች ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተመስገን ደበሎ (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው በሀገር በቀል እውቀቶች፣ በማዕድን፣ በግብርና፣ በእንስሳት ሀብትና በጤና ዘርፎች የጥናትና ምርምር ላይ ውጤታማ ሥራ እየሰራ ነው ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አቀፍ የጥናትና ምርምር አገልግሎትም የበርካታ ዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እመርታዊ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸውን የምርምርና የልማት ሥራዎች ለህዝብ በተሻለ ሁኔታ ለማድረስ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም የዩኒቨርሲቲውን ሥራዎች ለህዝብ በማስተዋወቅና የሀገርን ገጽታ በመገንባት ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተፈራ በቀለ በበኩላቸው፣ ኢዜአ የህዝብን አንድነትና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያጎለብቱ የዜናና ዜና ነክ ተግባራትን ለህዝብ እያዳረሰ ይገኛል ብለዋል።

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አቀፍ የልማት ሥራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የማይተካ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

በዚህም የኢዜአን የተደራሽነት አድማስ የበለጠ በማጠናከር የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የሚያፈልቃቸውን የጥናትና ምርምር ውጤቶች ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በቀጣይም የአካባቢውን እምቅ አቅሞችና ሀገር በቀል እውቀቶች ለማስተዋወቅ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የትብብር ስምምነት ሐምሌ 9 ቀን 2018 ዓ.ም በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የትብብር ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።

በትብብር ስምምነት መሰረት ዩኒቨርሲቲው በምርምርና በሀገር በቀል እውቀቶች ዙሪያ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ለህዝብ በተሻለ ሁኔታ ለማድረስ ጠቃሚ መደላድል ይፈጥራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም