የምክክር ጉባኤው በዜጎቿ መካከል ሀገራዊ መግባባት የሰፈነባት ጠንካራ ኢትዮጵያን በመገንባት ታሪካዊ ድርሻ እንደሚኖረው እምነት አለን - ተመካካሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባኤው በዜጎቿ መካከል ሀገራዊ መግባባት የሰፈነባት ጠንካራ ኢትዮጵያን በመገንባት ታሪካዊ ድርሻ እንደሚኖረው እምነት አለን - ተመካካሪዎች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በዜጎቿ መካከል ሀገራዊ መግባባት የሰፈነባት ጠንካራ ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ታሪካዊ ድርሻ እንደሚኖረው እምነት አለን ሲሉ ተመካካሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።
ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪሎችም በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።
በዚህ ታሪካዊ መድረክ የተሳተፉ ተመካካሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምክክሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን እኩል በማሳተፍ ሀገራዊ አንድነት በሚያጎለብት መልኩ እየተካሄደ ይገኛል።
ይህ የምክክር መድረክ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ አብሮነት እና ሕብረብሔራዊ አንድነትን እንደሚያጠናክር ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።
ከተመካካሪዎች መካከል ዳዊት ሙራ እንዳሉት፣ ምክክሩ በሀገሪቱ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ሂደቶች ውስጥ ሁሉም ዜጋ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ለማመቻቸት መሠረት እንደሚጥል አንስተዋል።
ለዘመናት የዘለቁ አለመግባባቶች እና ችግሮች በምክክር በመፍታት ለሀገራችን ብሩህ መጻኢ ዘመን ጠንካራ መሠረት የሚጣልበት ነው ብለዋል።
ሌላኛዋ ተመካካሪ ለምለም ጎበና በበኩላቸው፣ የምክክር መድረኩ እያንዳንዱ ተመካካሪ ሐሳቡን በስፋትና በጥልቀት ማቅረብ በሚችልበት መልኩ መካሄዱ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በምክክሩ የሚነሱ ሐሳቦች በሙሉ በተገቢው መንገድ የሚደመጡ በመሆኑ ለጋራ ሀገራዊ ግንባታ ጠንካራ ግብዓት ሆነው እንደሚያገለግሉ አንስተዋል።
ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚገኙበት መድረክ መሆኑ ደግሞ የምክክሩን አካታችነት እና አሳታፊነት በግልጽ የሚያሳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በነጻነት ሀሳቡን የሚያንሸራሽርበትና ድምፁ የሚሰማበትን እድል ፈጥሯል ያሉት ደግሞ ተመካካሪ ደፋለ መንሱር ናቸው።
ይህ ሀገራዊ የምክክር መድረክ እርስ በእርስ የመደማመጥና የመከባበር ባህልን በማጠናከር፣ ታላቋን ኢትዮጵያ በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባትና ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ እንደሚያስችል ተናግረዋል።