የምክክር ጉባኤው የወጣቶችን ተስፋ የሚያለመልም የመግባባት ምክረ ሀሳብ የሚፈልቅበት የጋራ መድረክ እንደሚሆን እንጠብቃለን - የአዲስ አበባ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባኤው የወጣቶችን ተስፋ የሚያለመልም የመግባባት ምክረ ሀሳብ የሚፈልቅበት የጋራ መድረክ እንደሚሆን እንጠብቃለን - የአዲስ አበባ ወጣቶች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የወጣቶችን ተስፋ የሚያለመልም ሀገራዊ የመግባባት ምክረ ሀሳብ የሚፈልቅበት የጋራ መድረክ እንደሚሆን እንጠብቃለን ሲሉ የአዲስ አበባ ወጣቶች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ በሚገኘው አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በሰፊ ተሳትፎና በጥልቅ ምክክር መካሄዱን ቀጥሏል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም በመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ በፖለቲካ ሥርዓት፣ በፖለቲካ ውክልናና በምርጫ ሥርዓት፣ በሙስናና በመልካም አስተዳደር፣ በሃይማኖት ጉዳዮችና በሰላም ግንባታ ዙሪያ በተካሄዱ ምክክሮች ተመካካሪዎች ባቀረቧቸው ምክረ ሀሳቦች ላይ መግባባት መደረሱን ይፋ አድርጓል።
ይህ ሂደት በተለይ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ተስፋን የሚያለመልም መሆኑን በአዲስ አበባ ኢዜአ ያነጋገርናቸው ወጣቶች ገልጸዋል።
እንደ ወጣቶቹ አስተያየት ምክክርና መደማመጥን የሚያስቀድሙ ሀገራዊ መድረክ ዘላቂ ሰላምን፣ ሀገራዊ መግባባትንና የጋራ የልማት ርዕይን ለመገንባት ጠንካራ መሠረት ይጥላል።
የአዲስ አበባ ነዋሪዋ ወጣት ልዩወርቅ ሙሉጌታ እንደገለጸችው፤ ምክክርን በማስቀደም ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚደረጉ ማንኛውም ዓይነት ጥረቶች የወጣቱን ተስፋ የሚያለመልሙ ናቸው።
ሀገር ስትመክር የተሻለች ኢትዮጵያን እንድናይ ያስችለናል ያለችው ወጣቷ፤ በምክክር የምትገነባ ሀገርም የዜጎቿን ዕድገትና ብልፅግና ለማሳለጥ ጠንካራ መደላድል መፍጠር እንደምትችል ገልጻለች።
የምክክር ጉባኤው የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት፣ በሰላም ግንባታና በልማት ሂደት ያላቸውን ተሳትፎ በማጠናከር ለቀጣዩ ትውልድ ተስፋ የሚሰጥ የጋራ መድረክ መሆኑንም ተናግራለች።
ከጉባኤው የሚፈልቁ የጋራ መግባባት ምክረ ሀሳቦችም ሰላምና አንድነቷን ጠብቃ ወደ ዘላቂ ዕድገትና ብልፅግና የምትራመድ ኢትዮጵያን ለመገንባት አጋዥ ሚና እንደሚኖራቸው ሀሳቧን አንስታለች።
ሌላው የመዲናዋ ወጣት ንጉሥ አይጋበዝ በበኩሉ፤ የምክክር ጉባኤው ቀጣዩ ትውልድ መደማመጥንና ምክክርን የአስተሳሰብና የኑሮ ባህል እንዲያደርግ ትልቅ መሠረት የሚጥል መሆኑን ተናግሯል።
በሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች መካከል የሚፈጠረው መግባባትና የሚቀርቡት ምክረ ሀሳቦችም በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም በመገንባት ሰላምን፣ አንድነትንና የጋራ ሀገራዊ ጥቅምን ለማስከበር ወሳኝ አበርክቶ እንደሚኖራቸው ገልጿል።
ሀገራዊ መግባባትን በመገንባት የወጣቶችን በሀሳብ የበላይነት፣ በሰላም የተመሠረተና የብልፅግና ርዕይ ያለው ሀገር መሻት ምላሽ ለመስጠት ጉባኤው ጠቃሚ መሆኑን ደግሞ ነብያት ስብሀቱ ተናግራለች።
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው ያለችው ወጣቷ፤ የጉባኤውን ሂደትም በሚገባ በመከታተል የጋራ መግባባት ውጤቶችን በጉጉት እየተጠባበቀች መሆኑን ገልጻለች።
ሌላኛው የአዲስ አበባ ወጣት አብነት ንጉሴ በበኩሉ፤ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የትውልድን የመመካከርና የመደማመጥ የአስተሳሰብ ባህል የሚያጎለብት የጋራ መድረክ ነው ብሏል።
በመደማመጥና በመመካከር ለዘመናት የቆዩ አለመግባባቶችንና ቁርሾዎችን በሰለጠነና ሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጉባኤው የሚያበረክተው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ገልጿል።