ቀጥታ፡

የአፍሪካ አቪዬሽን አርማ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቋማዊ ልህቀት በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዓይን

በሙሴ መለሰ

የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የአንድን ሀገር ኢኮኖሚያዊ ትስስር፣ የቱሪዝም ዕድገት እና የጂኦፖለቲካዊ ተፅዕኖ የመወሰን ከፍተኛ አቅም ያለው ስትራቴጂካዊ ዘርፍ ነው።

በአፍሪካ አህጉር በርካታ ሀገራት ብሔራዊ አየር መንገዶቻቸውን በትክክለኛ የንግድ መስመርና ጠንካራ ተቋማዊ መዋቅር ለመገንባት በሚታገሉበት በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሳየው ዘላቂ ዕድገትና ስኬት በመላው ዓለም ትልቅ አድናቆትንና ትኩረትን የሳበ አጋጣሚ ሆኗል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተመሠረተበትን 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በሚያከብርበት በዚህ ወቅት፣ ከትራንስፖርት ተቋም ከመሆን አልፎ የአፍሪካ አቪዬሽን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መሪ በመሆን ቁልፍ ሚናውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

ተቋሙ በተከተለው የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ፣ በሙያዊ አስተዳደር እና ባደራጀው ዘመናዊ የአቪዬሽን ማዕከል አማካኝነት ሀገሪቱን የአህጉሪቱ ዋነኛ አገናኝ ድልድይ እና የትራንዚት መዳረሻ ሆኗል።

ይህን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የላቀ ደረጃ የበለጠ ለማጠናከር እና የወደፊቱን የዓለም አቪዬሽን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ፕሮጀክት፣ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ ያላትን የመሪነት ሚና ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ግዙፍ መሠረተ ልማት ነው።

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ እየተገነባ የሚገኘው ይህ ሜጋ ኤርፖርት፣ የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድን የጭነትና የመንገደኞች ጫና በመቀነስ በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማስተናገድ አልሞ የተነሳ ነው።

ይህም ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ግዙፉ የአቪዬሽን ማዕከል በመሆን የቀጣናውን የቱሪዝም፣ የንግድና የሎጂስቲክስ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያነቃቃው ይጠበቃል።

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በሰሞኑ ዘገባቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድን ስኬት እና የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል።

የዩናይትድ ኪንግደሙ ዕለታዊ ጋዜጣ ዴይሊ ኤክስፕረስ (Daily Express) በዘገባው እንደጠቀሰው፣ ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በዓለም አቀፉ የዛሃ ሀዲድ አርክቴክቶች ዲዛይን የተደረገ ግዙፍ ፕሮጀክት እንደሆነ አመልክቷል።

አየር ማረፊያው እ.አ.አ. በ2030 በሚጠናቀቀው የመጀመሪያው ምዕራፍ 60 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም የሚኖረው ሲሆን፣ ይህም በዓመት 28 ሚሊዮን የሚያስተናግደውን የደቡብ አፍሪካውን ኦሊቨር ታምቦ እና 26 ሚሊዮን የሚያስተናግደውን የግብፁን ካይሮ ኤርፖርቶች በከፍተኛ ልዩነት በመብለጥ በአህጉሪቱ የመሪነቱን ቦታ እንደሚይዝ ገልጿል።

ፕሮጀክቱ አራት የመሬት ላይ የአውሮፕላን መነሻና ማረፊያ መንገዶችን፣ የ38 ኪሎ ሜትር ፈጣን የባቡር መስመር፣ የሆቴልና የንግድ ማዕከላትን ያካተተ በመሆኑ፣ የዓለም ኃያላን አገራትን፣ አሜሪካንና ቻይናን ጨምሮ፣ የዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን ትኩረት መሳቡን ዘገባው አመልክቷል።

ሌላኛው የዩናይትድ ኪንግደም ዕለታዊ ጋዜጣ ዴይሊ ሚረር (Daily Mirror) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት በኤርፖርት መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ በተቋማዊ የአመራር ዘዴው ለአህጉሪቱና ለሌሎች ሀገራት ትልቅ ተሞክሮ እንደሆነ ገልጿል።

ዲፕሎማት ካና ካናናታን በጋዜጣው ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ፣ አየር መንገዱ በመንግሥት ሥር ሆኖ ሳለ እ.አ.አ. በ2025/26 በጀት ዓመት 9.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘቱ፣ 20.7 ሚሊዮን መንገደኞችን ማጓጓዙ እና በ174 አውሮፕላኖች ወደ 150 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች መብረሩ “የመንግሥት ባለቤትነት የኪሳራ መንስኤ ነው” የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ያፈረሰ መሆኑን አመልክቷል።

እንደ ስሪላንካ ያሉ ሀገራት በየዓመቱ ብሔራዊ አየር መንገዶቻቸውን ከመንግሥት ግምጃ ቤት ለመደጎም ሲታገሉ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነፃ በሆነ የንግድ ስትራቴጂ መመራቱ የስኬቱ ምሥጢር መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ የአቪዬሽን አመራር ልህቀት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያደገ መምጣቱ በጽሑፉ ላይ ሰፍሯል።

በተመሳሳይ መልኩ ዘ ኢስት አፍሪካን (The East African) ላይ በቻርልስ ኦንያንጎ-ኦቦ የቀረበው ጽሑፍ እንደሚያስረዳው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበላይነት የመጣው በጠንካራ የቴክኒክ ሥልጠና፣ በአውሮፕላን ጥገና ልህቀት፣ በረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ፣ በተቋማዊ አሠራር እና በጠንካራ ዲሲፕሊን የሚመራ በመሆኑ ነው።

አየር መንገዱ የራሱን ስኬት ከማስመዝገብ ባለፈ፣ የቀድሞና የአሁኑ አመራሮቹን እንደ ASKY፣ Malawi Airlines፣ Air Congo፣ Zambia Airways፣ Uganda Airlines እና RwandAir ባሉ በርካታ የአፍሪካ አየር መንገዶች ውስጥ በቁልፍ የካፒቴንነትና የአመራር ቦታዎች ላይ በመመደብ የመላው አፍሪካ አቪዬሽን አቅም እንዲገነባ መሠረት መሆኑን ጽሑፉ አመልክቷል።

ታይምስ ኩዌት (The Times Kuwait) ባወጣው መረጃ መሠረት፣ እ.አ.አ. 1945 የተመሠረተው ይህ አየር መንገድ የ80 ዓመታት የልህቀት ጉዞውን በሚያከብርበት በዚህ ወቅት በስካይትራክስ (SKYTRAX) ዘንድ ለስምንት ተከታታይ ዓመታት “የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ” በመባል መመረጡን ገልጿል።

አየር መንገዱ አዲስ አበባን የትራንዚት ማዕከል በማድረግ መንገደኞች በቆይታቸው እንደ እንጦጦ ፓርክ፣ አንድነት ፓርክ፣ ወንጪ ሐይቅ፣ ጨበራ ጩርጩራ፣ ላሊበላን  እና የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ ሌሎች የመስብ ቦታዎችን እንዲጎበኙ በማስቻል የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ እያነቃቃ እንደሚገኝ ጠቅሷል።

በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት የአንድ ሀገር ተቋም ጥንካሬ ማሳያ ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ በሙያዊ አመራርና በረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ከተመራ ምን ያህል ስኬታማ መሆን እንደሚችል ያሳየ ትልቅ ተሞክሮ ነው።

በቢሾፍቱ እየተገነባ የሚገኘው አየር ማረፊያ ሲጠናቀቅ የመንገደኞችን የማስተናገድ ጫና በመቀነስ፣ የአህጉሪቱን የንግድ፣ የሎጂስቲክስና የቱሪዝም ትስስር ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል።

ይህ የራዕይና የተቋማዊ ጥንካሬ ቅንጅት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ካርታ ላይ ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ይበልጥ የሚያጠናክረው ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም