በሸገር ከተማ በምግብ ራስን ለመቻል የሚያስችሉ የግብርና ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ በምግብ ራስን ለመቻል የሚያስችሉ የግብርና ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው
ሸገር ፤ነሐሴ 6/2018 (ኢዜአ)፡– በሸገር ከተማ ተረጂነትን ለማስወገድ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተያዘውን በምግብ እህል ራስን የመቻል ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችሉ የግብርና ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ በምግብ እህል ራስን ለመቻል እና የስንዴ ምርትን ከውጭ ማስገባትን ለማስቆም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስፋት እየተገበረችው የሚገኘው የኩታገጠም እርሻ ውጤት እያስገኘ ነው።
የሸገር ከተማ አስተዳደርም በከተማ ዙሪያ የሚገኙ የእርሻ መሬቶችን በዘመናዊ አሰራር በማልማት ተረጂነትን ለማስወገድ እና የከተማዋን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
በከተማዋ ኩራ ጂዳ ክፍለ ከተማ በ340 ሄክታር መሬት ላይ በኩታገጠም አሰራር ለምርጥ የስንዴ ዘር ብዜት የሚሆን የዘር መዝራት ስራ ዛሬ ተከናውኗል።
ይህን ዓላማ ለማሳካት ዋናው ማነቆ የሆነውን የምርጥ ዘር እጥረት ለመቅረፍ፣ ዛሬ በኩራ ጂዳ ክፍለ ከተማ የተካሄደው የ340 ሄክታር መሬት ኩታገጠም ዘመቻ ጥራት ያለው የስንዴ ዘር በማባዛት ለአካባቢውና ለሌሎች አራሾች ለማቅረብ ያለመ ነው።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሸገር ከተማ የግብርና እና ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ ግርማ ሀይሉ እንደገለጹት፤ በከተማዋ ምርታማነትን በማሳደግ በግብርናው ዘርፍ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት በሰፊው በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
በተለይም በከተማዋ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የውጭ ኤክስፖርትን ማሳደግ እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የመተካት ዕቅዶችን ለማሳካት በትኩረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ለከተማዋ አርሶ አደሮች የክህሎት ሥልጠና በመስጠት የሥራ ባህልን መለወጥ ተችሏል ብለዋል።
ዛሬ የተካሄደው ስንዴን በኩታ ገጠም ማሳን በዘር የመሸፈን ዘመቻም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
የዛሬው ስንዴን የመዝራት ዘመቻ የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በሙሉ በመጠቀም የተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚሁ መሠረት በከተማዋ በዘንድሮው የመኸር እርሻ ወቅት 70 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታገጠም ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
የሸገር ከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደጀኔ በቀለ በበኩላቸው፤ በከተማዋ የምርት እና የምርታማነት መጠንን ለማሳደግ ዘንድሮ እየተከናወነ ካለው የግብርና ሥራ ውስጥ እስካሁን 55 በመቶ የሚሆነው ሙሉ የግብርና ፓኬጅ በመጠቀም እንዲለማ መደረጉን ገልጸዋል።
በከተማዋ የኩራ ጂዳ ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ አቶ ተማም ሁሴን፤ በክፍለ ከተማው እየለማ ካለው አጠቃላይ መሬት ውስጥ ስንዴ በኩታገጠም የማልማቱ ስራ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።
የኩታገጠም እርሻ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ ምርትና ምርታማነታቸውን እንዳሳደገላቸው የተናገሩት ደግሞ በዘር ብዜቱ ተሳታፊ አርሶ አደሮች ናቸው።