የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በድሬዳዋ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በድሬዳዋ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማ እያደረገ ነው
ድሬደዋ፤ ነሐሴ 6/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማ እያደረገ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ገለጹ።
በድሬዳዋ አስተዳደር በከፊል ወደ ስራ የተሸጋገሩ ስምንት አምራች ኢንዱስትሪዎች ተጎብኝተዋል ።
ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በወቅቱ እንዳሉት በከተማ አስተዳደሩ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ የተደረጉ የተቀናጁ ድጋፎችና ክትትሎች ውጤት እያመጡ ነው።
የመሬት፣ የኤሌክትሪክ፣ የፋይናንስ፣ የመሠረተ ልማት እና ሌሎች ጥያቄዎች በአፋጣኝ እንዲመለሱ በማድረግ ኢንዱስትሪዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ አስችሏል ብለዋል።
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት አመት ብቻ 11 ከፍተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ በመግባት ከ1ሺ 400 በላይ የቋሚ የስራ ዕድል መፍጠራቸውን አንስተዋል ።
ኢንዱስትሪዎቹ ተኪ ምርቶች ከማምረት በተጨማሪ የወጪ ምርቶችን በማምረት ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ምንዛሬ እያስገኙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የዛሬው ጉብኝትም እየተደረገ የሚገኘውን የድጋፍና የክትትል ስራ በማጠናከር በከፊል ማምረት የጀመሩትን አምራች ኢንዱስትሪዎች በሶስት ወራት ውስጥ ወደ ሙሉ አገልግሎት እንዲገቡ ለማስቻል መሆኑን አመላክተዋል።
ጉብኝት ከተደረገባቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል የሳሙና ፣ የጭማቂ፣ የውሃ፣ የሮቶ፣ የካርቶንና፣ የእርሻ መሳሪያ ማምረቻዎች እንዲሁም የቡና ማቀነባበሪያዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ኢንደስትሪዎችን ምርታማ ለማድረግ የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረጉን ያነሱት ደግሞ የኤስ ስቲል አምራች ኢንዱስትሪ ባለቤት አቶ ሰለሞን ተስፋዬ ናቸው።
ኤም ኮፊ ቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል አብዱረህማን በበኩላቸው ለቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካቸው የማስፋፊያ ቦታ ጥያቄ በአንድ ወር ውስጥ ምላሽ ማግኘታቸው ስራቸውን ለማሳካት እንዳገዛቸው ጠቁመዋል።
የቡና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ መካከለኛ እና ሩቅ ምስራቅ ገበያ በመላክ ተወዳዳሪ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።