ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ከ173 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ተሰጠ

ደሴ፤ነሐሴ 6/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ173 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠቱን የክልሉ መሬት ቢሮ አስታወቀ።

በደሴ ከተማ አስተዳደር የገጠር ቀበሌ አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ዛሬ ተካሂዷል።


 

በሥነ- ሥርዓቱ ላይ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ እንደገለጹት፤ የክልሉን መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም በማዘመን የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት የአርሶ አደሮችን ዘላቂ የመሬት ባለቤትነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤት እንዳስገኘ ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ ከ488 ሺህ በላይ የመሬት ይዞታዎች ላይ የሁለተኛ ደረጃ ማረጋገጫ ደብተር መስጠት መቻሉን ገልጸዋል።

የይዞታ ደብተሩ የአርሶ አደሩን ይዞታ በዘመናዊ መንገድ በመለካትና ማረጋገጫ በመስጠት የብድርና ሌሎች አገልግሎቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ  ሰፊ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም አመልክተዋል።

እንዲሁም ቀደም ሲል በመሬት ወሰንና ድንበር አካባቢ የሚፈጠሩ ግጭቶችን፣ አለመግባባቶችንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከማስቀረቱ ባለፈ ትክክለኛ ግብር መክፈል እንዲቻል የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ43 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተራቸውን ዋስትና በማስያዝ ከ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መውሰዳቸውን ገልጸዋል።


 

በዛሬው ዕለትም በደሴ ከተማ አስተዳደር ለ996 አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መስጠት መቻሉን ገልጸው፣ በአዲሱ በጀት ዓመትም ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፤ በከተማው የገጠር መሬት አያያዝና አጠቃቀምን በማዘመን የአርሶ አደሩን የመሬት ባለቤትነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

መሬቱን በሳይንሳዊ መንገድ በመለካት ትክክለኛ መገኛውን፣ ድንበሩን፣ ወሰኑንና መጠኑን በማስቀመጥ ለአርሶ አደሩ የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እየተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።


 

ይህም ሕገ-ወጥ መሬት ወረራንና ግንባታን በማስቀረት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እያቃለለ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በደሴ ከተማ የዋሊዶ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አሊ ሁሴን እና ወይዘሮ ደመቁ ሁሴን፤ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ማግኘታችን መሬቱን በተሻለ መንገድ ለማልማትና ተጨማሪ ሀብት ለማፍራት ያስችለናል ነው ያሉት።

የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተሩ ወሰንና ልኬትን በትክክል ያስቀመጠ በመሆኑ የመሬታችንን ዘላቂ ዋስትና እና ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የክልልና የከተማ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም