ቀጥታ፡

የወጣቶችን አቅምና እውቀት በማስተባበር ሁለገብ ልማትን ማፋጠን አለብን

ገንዳ ውኃ፣ ነሐሴ 6/2018  (ኢዜአ)፡-የወጣቶችን አቅምና እውቀት በማስተባበር የአካባቢውን ሁለገብ ልማት ማፋጠንና ህዝባዊ አንድነትን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ ገለጹ። 

"ብዙኃን የወጣቶች እውቀት ለጋራ ትልም" በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ ተከብሯል።


 

ዕለቱ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችና በተለያዩ ሁነቶች በድምቀት የተከበረ ሲሆን፣ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችና የመሠረተ ልማት አውታሮች ተጎብኝተዋል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ እንዳሉት፤ ወጣቶች በአካባቢው የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን በማፋጠን፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በማጠናከርና ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ የጎላ ሚና አላቸው። 

በተለይም የሀገር ህልውና፣ የልማትና የለውጥ ዋና ኃይል በመሆናቸው፤ እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውንና ፈጠራቸውን በማስተባበር ለአካባቢው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት በግንባር ቀደምነት ሊሰለፉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳለው ማሩ በበኩላቸው፤ ወጣቶችን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ ዘርፎች የነቃ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ወጣቶች በመልካም ሥነ-ምግባር ታንጸው ሀገራዊ አንድነትን እንዲገነቡና ከአሉታዊ አስተሳሰቦች ርቀው የልማት አርበኛ እንዲሆኑ ከአጋር  አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም አብራርተዋል።

በበጎ ፈቃድ ሥራው የተሳተፈው ወጣት ያለው ተረፈ፤ "ያለብንን የዜግነት ግዴታ በመወጣት ለአካባቢያችን ልማትና አንድነት በቁርጠኝነት መሥራታችንን እንቀጥላለን" ብሏል።

አክሎም ወጣቱ የሀገር ተረካቢ እንደመሆኑ መጠን ከአሉታዊ እንቅስቃሴዎች በመውጣት አቅሙንና እውቀቱን ለአካባቢው ሰላም፣ ልማት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ማዋል እንዳለበት አስገንዝቧል።

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት አክማዝ ገብሬ በበኩሏ፤ "አንድነታችንን በማጠናከርና እርስ በእርስ በመደጋገፍ ለአካባቢያችን ሁለገብ እድገት መሥራት ይጠበቅብናል" ስትል ተናግራለች። 

በተለይም በበጎ ፈቃድ አገልግሎትና በማኅበራዊ ሥራዎች ላይ የሚደረገውን ርብርብ በማጠናከር ሕብረተሰቡን ለመደገፍና የዞኑን መልካም ገጽታ ለመገንባት እንደሚሠሩ አስረድታለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም