የወጣቶች ወርቃማ የስነ-ህዝብ ዕድል፦ ለአዲስ ታሪክ ግንባታና ለሀገራዊ ብልጽግና - ኢዜአ አማርኛ
የወጣቶች ወርቃማ የስነ-ህዝብ ዕድል፦ ለአዲስ ታሪክ ግንባታና ለሀገራዊ ብልጽግና
በሙሴ መለሰ
የዓለም የወጣቶች ቀን መነሻ ታሪኩ የሚጀምረው እ.ኤ.አ. በ1991 (በኢትዮጵያ 1983 ዓ.ም) በኦስትሪያ ቪዬና በተካሄደው የመጀመሪያው የዓለም የወጣቶች ፎረም ላይ ነው።
በወቅቱ የተሰበሰቡት ወጣት ተወካዮች በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጣቶች ድምፅ የሚሰማበትና ትኩረት የሚያገኝ ልዩ ቀን እንዲኖር ሀሳብ አቀረቡ።
ይህ ሀሳብ ዳብሮ እ.ኤ.አ. በ1998 በሊዝበን ፖርቱጋል በተካሄደው የዓለም የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴሮች ጉባኤ ላይ ውሳኔ ሆኖ ቀርቧል።
ይህን ተከትሎም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እ.አ.አ በ1999 ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት በየዓመቱ ኦገስት 12 (ነሐሴ 6) ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ሆኖ እንዲከበር ተወስኗል።
የመጀመሪያውም እ.አ.አ በ2000 ተከበረ። የቀኑ ዋና ዓላማ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች በመዳሰስ፣ ለዓለም ሰላምና ዘላቂ ልማት የሚያበረክቱትን የፈጠራና የልማት አቅም እውቅና መስጠት ነው።
ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ “ብዝሃ የወጣቶች እውቀት፤ ለጋራ ትልም!” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ ለ27ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
መሪ ሀሳቡ በዓለም ዙሪያ የሚገኘው ወጣት የተለያየ ባህል፣ አካባቢና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ቢኖረውም፣ የተሻለ ወደፊት የመገንባት፣ የትምህርት፣ የስራ እና የሰላም የጋራ ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት “ብዝሃ የወጣቶች እውቀት፤ ለጋራ ትልም!” በሚል ሀገራዊ ጭብጥ ለ23ኛ ጊዜ እየተከበረ ሲሆን፣ ይህም የሀገሪቱን ወጣቶች ልዩ ልዩ እውቀት፣ ክህሎትና አቅም በማስተባበር ለጋራ ሀገራዊ ዕድገት ማዋል እንደሚገባ ጥሪ የሚያቀርብ ነው።
ይህ ዕለት ለኢትዮጵያ ልዩና ታሪካዊ ትርጉም አለው፤ ምክንያቱም ከኢትዮጵያ ህዝብ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ዕድሜው ከ35 ዓመት በታች በመሆኑ ኢትዮጵያ እጅግ ግዙፍ የሆነ ወርቃማ የስነ-ህዝብ ዕድል (Demographic Dividend) ባለቤት ናት።
ይህን አቅም በተገባ መንገድ በመጠቀም ወጣቱን በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ በማክሮ-ኢኮኖሚ ግንባታ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በበጎ አድራጎት እና በፈጠራ ስራዎች ላይ ማሰማራት የሀገሪቱ የብልጽግና ዋና ምሰሶ ያደርገዋል።
በመሆኑም ወጣቱን በችግር ጊዜ ብቻ ትኩረት የሚሰጠው አካል ሳይሆን፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ቆሞ በጋራ የሚቀርጽ ግንባር ቀደም ኃይል የማድረግ የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል።
ይህንን ሀገራዊ እውነታ እና የወጣቱን ቁልፍ ሚና አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያን ከወጣቶቿ ነጥሎ ማየት አይቻልም ሲሉ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ወጣት መልካም ዓላማን አንግቦ የሚንቀሳቀስ፣ የለውጥ ዋነኛ ሞተር እና የሀገራችን ሉዓላዊነት ጽኑ ማገር ነው።
የአሁኑ ወጣት ሀገራችንን የኋሊት ጠፍንገው የያዟትን አጓጉል ልማዶች፣ አላስፈላጊ ንትርኮች፣ ጭቅጭቅ እና ግጭቶችን በመራቅ በልማት ላይ አተኩሯል፤ ድህነትንም ተጠይፎ የሀገሩን ታሪክ በአዲስ ብዕርና ብራና እየጻፈ ይገኛል።
የመደመር መንግሥት የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና የአመራርነት ሚና ለማጠናከር በትኩረትና በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
ሀገራዊ ርዕያችንን ዕውን ለማድረግም ሁሉም በንቃት እየተጋ በፍቅር እንዲመላለስ ጥሪ በማቅረብ፣ ወጣቱ በሀገሪቱ የወደፊት ጉዞ ላይ ያለውን የማይተካ ድርሻ በአፅንኦት አጉልተዋል።
በአጠቃላይ፣ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ለኢትዮጵያ ወጣቶች ቀኑን አስታውሰው የሚያልፉበት ብቻ ሳይሆን፣ የተጣለባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት የሚያስታውሱበት እና አቅማቸውን የሚያድሱበት መልካም አጋጣሚ ነው።
የኢትዮጵያ የወደፊት ብልጽግና እና ዘላቂ ሰላም እውን የሚሆነው የወጣቶችን እውቀት፣ ጉልበት እና የፈጠራ አቅም በአንድነት አስተባብሮ መጠቀም ሲቻል ብቻ ነው።
በዲጂታል ፈጠራ፣ በአረንጓዴ ልማት እና በማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ የወጣቱ ንቁ ተሳትፎ መቀጠል የነገዋን የበለፀገች ኢትዮጵያ በጋራ የመገንባቱን ሂደት ያፋጥነዋል።