ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር መሠረት ይጥላል

ወላይታ ሶዶ፤ ነሐሴ 6/2018 (ኢዜአ)፡-ሀገራዊ ምክክሩ ለቆዩ አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሄ ከመስጠት ባለፈ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር መሰረት ይጥላል ሲሉ የወላይታ ዞን የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቁ ችግሮችን በመፍታት ሀገራዊ አንድነትን እንደሚያጠናክር የታመነበት ሀገራዊ ምክክር የተለያዩ ሂደቶችን አልፎ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የማጠቃለያ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ነው። 

ምክክሩ ሰላምና ልማትን በዘላቂነት በማስፈን ለሁሉም የምትመች ሀገር በመገንባት ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል፡፡

ምክክሩን አስመልክቶ ኢዜአ በወላይታ ዞን ያነጋገራቸው የሀገር ሽማግሌዎች እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ የነበራቸውን የመመካከርና አብሮ የመኖር እሴት በማስቀጠል ልዩነቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ምክክሩ አስፈላጊ ነው።

ከሀገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ ጌታቸው መና፤ ምክክሩ እኔ አውቅልሃለሁ እሳቤን አስቀርቶ በተለያዩ ማህበራዊ መሰረቶች ያሉ ዜጎችን በማካተት መካሄዱ ለኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ትልቅ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያውያን መካከል ለዘመናት መተማመንን ያሳጡ አለመግባባቶችና ቁርሾዎችን በመፍታት ሀገራዊ አንድነትን የማጠናከር አቅሙ የጎላ በመሆኑ ለትውልድ የተሻለች ሀገር መፍጠር ያስችላል ብለዋል።

በሀገሪቱ ለቅራኔ ምንጭ የነበሩ የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከማስቻሉ ባለፈ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር መሰረት ይጥላል ብለዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች እየተሸረሸረ የመጣው አብሮነትና የሰላም እጦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉን ያሳተፈ ምክክር ማድረግ ሚናው የጎላ ነው ያሉት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የሀገር ሽማግሌ አቶ ኢያሱ ጋጃቦ ናቸው።

ወደማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርም ታሪካዊ አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸው፣ በጉባኤው ውይይት እየተደረገባቸው ያሉ ስምንት አጀንዳዎች የህዝብ ሀሳቦች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአጀንዳዎቹ ላይ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተመካካሪዎች ጥልቅ ውይይቶችን በማድረግ በቀጣይ ለሀገርና ለህዝብ ይጠቅማል የሚል ምክረ ሀሳቦችን ያስቀምጣሉ የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ተወካዮቻቸውም በምክክሩ በመሳተፍ ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረው፣ በጋራ መክሮ የሚሰራ ሥራ ውጤቱ ይሰምራል ብለዋል። 

የዘመናት ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ በሀገራዊ ምክክር እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ለሀገር ሰላምን ከማጽናት ባለፈ ከሀይል ይልቅ ችግሮችን በውይይት መፍታትን ባህሉ ያደረገ ትውልድ ለመፍጠር ያስችላል ሲሉም ገልጸዋል 

"ሁላችንም ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ ሀገር የለንም" ያሉት አቶ ኢያሱ ምክክር ስር የሰደዱ ችግሮቻችንን በመፍታት ለሁላችንም የምትመች ሀገር ለመገንባት ስለሚያስችል ይህን ታሪካዊ እድል ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።

አቶ ፒኖ ማኖ የተባሉ ሌላኛው ሀገር ሽማግሌ በበኩላቸው አለመግባባቶችን ለመፍታት ጠረጴዛ ዙሪያ መሰባሰብ የመመካከር ባህልን የሚያሳድግና የተሻለች ሀገር ለትውልድ ለማቆየት ያስችላል፡፡

በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም በወኪሎቹ አማካይነት እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ለዘመናት ላለመተማመንና ለልዩነት ምንጭ  በሆኑ ችግሮች ላይ በጋራ መክሮ መፍትሄ ለመስጠት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። 

ጠንካራ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠርና ቂምና ቁርሾዎችን በማስቀረት አንድነቷ የጸና ሀገር ለመገንባት ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የምክክር ሂደቱን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የምክክር ሂደቱ እየተጠናከረና ወደ ማጠቃለያ ምዕራፍ እየተሸጋገረ እንደሚገኝ መናገራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም