የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች በተቀናጀ መልኩ ማህበራዊ ችግሮችን ለማቅለል እያገዙ ነው-አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች በተቀናጀ መልኩ ማህበራዊ ችግሮችን ለማቅለል እያገዙ ነው-አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ
ሰመራ፣ነሀሴ 6/2018 (ኢዜአ) ፡-የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተቀናጀ መልኩ ማከናወን መቻሉ ማህበራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እያገዘ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ አስታወቁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ የ2018 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትና የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በዱብቲ ወረዳ አሮላፍና ገበላይቱ ቀበሌ አካሒደዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲኤታዎች አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እና አምባሳደር ሐድራ አበራ፤ የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት ቢሮ ኀላፊ አቶ ኡመር ኑርን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እንዳሉት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመተባበር ዜጎች የሚገጥሟቸውን ማህበራዊ ችግሮች ከማቃለል አንፃር ውጤት እየተመዘገበበት ይገኛል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በዘንድሮው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአፋር ክልል 10 የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት ግንባታ ለማከናወን ወደ ስራ መግባቱን ገልፀዋል።
በመርሃ ግብሩ ከመኖሪያ ቤቶቹ በተጨማሪ አንድ የመዋዕለ ህፃናት ትምህርት ቤትም እንደሚገነባም ነው የገለጹት።
የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት ቢሮ ኀላፊ አቶ ኡመር ኑር ፤በበኩላቸው በክልሉ የተጀመረው የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል።
የበጎ ፈቃደኞች ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱም የህብረተሰቡን የመረዳዳት ባህል ይበልጥ እያጠናከረው መምጣቱን ነው የተናገሩት።