በምክክሩ ኢትዮጵያን የሚገነቡ ጠንካራ ሀሳቦች እየተንጸባረቁ ነው- ተመካካሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በምክክሩ ኢትዮጵያን የሚገነቡ ጠንካራ ሀሳቦች እየተንጸባረቁ ነው- ተመካካሪዎች
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 6/2018(ኢዜአ) ፦በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያን የሚገነቡ እና ወደፊት የሚያራምዱ ጠንካራ ሀሳቦች እየተንጸባረቁ መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።
ዋናው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ በሚገኘው አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በምክክሩ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ እየመከሩ ይገኛሉ።
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ለዘመናት ለዘለቁ አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሔ በማበጀት ሰላም እና መግባባት የሰፈነባትን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ መሠረት እንደሚጥል ይታመናል።
በመድረኩ የተሳተፉ ተመካካሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፣ ይህ ስልጡን አካሄድ ኢትዮጵያውያንን ይበልጥ በማቀራረብ ጠንካራ የዴሞክራሲ እና የምክክር ባህልን እንደሚያጎለብት ተናግረዋል።
የ6ኛው ዙር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባል መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በምክክሩ ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያራምዱ እና የቆዩ ችግሮቻችንን ሊፈቱ የሚችሉ ምክረ ሀሳቦች እየተንጸባረቁ ይገኛሉ።
ምክክሩ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ እና እንደ ሀገር የሚያስማሙንን ጉዳዮች የጋራ እያደረግን ለመቀጠል ትልቅ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሂደቱ ተሳታፊ መሆናቸው ሀገራዊ የፖለቲካ ባህላችን ምክክርን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን ገልጸዋል።
የታሪክና የፖለቲካ ሳይንስ መምህር እንዲሁም ተመካካሪው አልአዛር ዓባይነህ በበኩላቸው፤ ለዘመናት በዘለቁ አለመግባባቶች ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ስትፈተን መቆየቷን አስታውሰው፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከምክክር ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ገልጸዋል።
የምክክር ጉባኤው በሀገራዊ መግባባት የጸናች ኢትዮጵያን ለመገንባትና ለመጪው ትውልድ ብሩህ መሠረት ለመጣል ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በምክክሩ ለሀገር የሚጠቅም ሐሳብ በማበርከት የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ አካል በመሆናቸው ኩራት እንደሚሰማቸውም ገልጸዋል።
ይህ ወቅት በሀገሬ ያለኝ ተስፋ እጅግ የለመለመበት ወቅት ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ እና የሕግ ባለሙያ ወንድሙ ግዛው ናቸው።
ፍትሕ እና እኩልነት የሰፈነባትን የተሻለች ኢትዮጵያ ለትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ተመካካሪ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን መመልከታቸውንም አንስተዋል።