ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው በመደማመጥ ላይ የተመሰረተ መግባባትን በመገንባት የጋራ አሸናፊነትን የሚያቀዳጅ አካታች መድረክ ነው

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 6/2018(ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የዘመናት ልዩነትና አለመግባባትን በሰለጠነ የመደማመጥ ምክክር ወደ የጋራ መግባባትና የጋራ አሸናፊነት የሚያቀዳጅ አካታች መድረክ መሆኑን ተመካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።

በጉባኤው በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።

በመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ በፖለቲካ ሥርዓት፣ በፖለቲካ ውክልናና በምርጫ ሥርዓት፣ በሙስናና በመልካም አስተዳደር፣ በሃይማኖት ጉዳዮችና በሰላም ግንባታ አጀንዳዎች ላይ ተመካካሪዎች ባቀረቧቸው ምክረ ሀሳቦች መግባባት ላይ መድረሳቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይፋ አድርጓል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመካካሪዎች እንዳሉት፣ ሀገራዊ ምክክሩ መደማመጥና መከባበርን መሠረት በማድረግ እየተካሄደ በመሆኑ የጋራ መግባባትን ለመገንባት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

ተመካካሪና የጉምዝ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀ መንበር ግራኝ ጉደታ እንደገለጹት፣ የምክክር ጉባኤው የጋራ መግባባትን በሚገነቡ አካታችና አሳታፊ ሃሳቦች እየተንጸባረቁበት ነው።

ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ወኪል ተመካካሪዎች ለሀገር የሚጠቅሙ የተለያዩ ሀሳቦችን በነጻነትበማቅረብ የጋራ ምክክር እየተካሄደባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የምክክር ሂደቱ ለረጅም ዓመታት የቆዩ ችግሮችን ለመፍታትና ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

ሌላው ተመካካሪና የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት ሊቀመንበር ገብሩ በርሔ በበኩላቸው፣ የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በውይይት የሚያምን ትውልድና ማኅበረሰብ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

ምክክር ለትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማሸጋገር የሚያግዝ የጋራ መድረክ ነው ያሉት አቶ ገብሩ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤም መግባባትን የሚገነባ ምክክር እያደረገ ነው ብለዋል።

ተመካካሪ ነስሩ ዑዳ በበኩላቸው፣ በጉባኤው የምንመክርባቸው ዐበይት አጀንዳዎች የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ለመገንባት የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።


 

በ10፣ በ50፣ በ250 እና በ500 የምክክር ቡድኖች ደረጃ እየተካሄደ የሚገኘው የምክክር መድረክ የጋራ መግባባትን የሚገነቡ ሃሳቦች እየቀረቡበት መሆኑን ገልጸዋል።

በምክክሩ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተወከሉ ተመካካሪዎች ሰፊ ምክክር እያደረጉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

የምክክር ሂደቱ አካታችና አሳታፊ ነው ያሉት ተመካካሪዋ፤ ተመካካሪዎች የተለያዩ ሀሳቦችን በመከባበርና በመደማመጥ በማንሳት የጋራ መግባባት የሚገነባ ምክክር እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም