ሀገራዊ ምክክሩ መግባባት የሰፈነባት እና ብሩህ ተስፋ ያላትን ሀገር እንደሚፈጥር ጽኑ እምነት አለን - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ መግባባት የሰፈነባት እና ብሩህ ተስፋ ያላትን ሀገር እንደሚፈጥር ጽኑ እምነት አለን
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 6/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የዘለቁ ችግሮችን በሰለጠነ ምክክር የፈታች፣ መግባባት የሰፈነባት እና ብሩህ ተስፋ ያላትን ሀገር እንደሚፈጥር ጽኑ እምነት እንዳላቸው ተመካካሪዎች ገለጹ።
ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ተወካዮች የተሳተፉበት፣ በስምንት ዋና ዋና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የሚያተኩረው እና ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።
ምክክሩ ኢትዮጵያዊያን በባለቤትነት መንፈስ የሀገራቸውን የነገ ብሩህ ዕጣ ፈንታ እንዲወስኑ እና ሀገራዊ መግባባት የሰፈነባትን ሀገር መገንባት የሚያስችል ታሪካዊ ዓላማን ሰንቋል።
በሂደቱ እየታየ ያለው ሰፊ አካታችነት፣ አሳታፊነትና የዜጎች ተነሳሽነትም ችግሮችን በሰለጠነ የምክክር አግባብ ለመፍታት በህዝብ ዘንድ ትልቅ ተስፋን የፈነጠቀ ሆኗል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ተወካይ ተመካካሪዎች፣ ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት መሠረት የሚጥሉ እና የጋራ መግባባትን የሚያጠናክሩ የፖሊሲ ምክረ ሀሳቦች የሚፈልቁበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሂደቱ የሚደረሱት ስምምነቶችም ሕብረብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ተመካካሪው ዮሐንስ በንቲ( ዶ/ር)፤ ምክክሩ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የሙያ ማኅበራት፣የሃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ነው ብለዋል።
ተመካካሪዎች በቡድኖች ተደራጅተው ውይይት ማካሄዳቸው ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲገልጹና አሳታፊ የውይይት ምህዳር እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸዋል ።
ሂደቱ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማት እና አብሮነት መሠረት የሚጥሉ የፖሊሲ ምክረ ሀሳቦች የሚፈልቁበት መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ቦርድ አባል ተመካካሪው ኢንጂነር አለማየሁ ንጋቱ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የዘለቁ ችግሮችን በሰለጠነ ምክክር የፈታች፣ መግባባት የሰፈነባት እና ብሩህ ተስፋ ያላትን ሀገር እንደሚፈጥር ጽኑ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ህዝብ ለልማት በጋራ የሚነሳበት አውድ በመፍጠርም የተረጋጋች እና ዘላቂ ሰላም ያላት ሀገር ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገር ሽማግሌዎች መማክርት የቦርድ አባል ተመካካሪው ሀጂ ሙፍቲ ዑመር ፤ እስካሁን የነበረው የምክክር ሂደት እጅግ አሳታፊ እና ለጠንካራ ሀገር ግንባታ ወሳኝ ሚና የሚጫወት ነው ብለዋል።
ምክክሩ የተሳካ ውጤት እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸው፤ የኢትዮጵያዊያንን አብሮነት ይበልጥ የሚያጠናክር እና የሚያስተሳስር መሆኑን ተናግረዋል፡።