የምክክር ጉባኤው የዘመናት ቅሬታና ስብራትን በመጠገን ሀገርን የሚያሻግር የተስፋ መድረክ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባኤው የዘመናት ቅሬታና ስብራትን በመጠገን ሀገርን የሚያሻግር የተስፋ መድረክ ነው
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 6/2018 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የዘመናት ሀገራዊ ቅሬታና ስብራትን በሰለጠነ ምክክር በመጠገን ወደ መግባባት የሚያሻግር የተስፋ መድረክ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው አሳታፊና አካታችነት ሁሉም ዜጋ አለኝ የሚለውን ጉዳይ በግልጽ የሚያንጸባርቅበትን ዕድል ፈጥሯል።
ይህም የጋራ መግባባትን መገንባት የሚያስችል ምክክር በማካሄድ አንዱ የአንዱን ሀሳብ የሚገነዘብበትን ዕድል በመፍጠር ሀገር የሚያሻግር ምክረ ሀሳብ ለማፍለቅ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በምክክር ሂደት የሀገር ሽማግሌና የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር አሕመድ ዘከሪያ እንዳሉትም፤ ኢትዮጵያ በሰለጠነ የምክክር መድረክ የጋራ መግባባት የሚሹ በርካታ የታሪክ ስብራቶች ያሉባት ሀገር ናት ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤም በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምክክር በማካሄድ የሁሉንም አሸናፊነት የሚያቀዳጅ የጋራ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር ጉባኤውም ከታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል ጀምሮ በአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የቅድመ ምክክር ጉባኤ ወቅት አካታችና አሳታፊ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
በዚህም በዋናው የምክክር ጉባኤ ላይ የ130 ሚሊዮን ህዝብ ወኪል የሆኑ አራት ሺህ የኢትዮጵያውያን ተመካካሪዎች ግልጽ፣ አሳታፊና አካታች ምክክር እያደረጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በምክክር ለትውልድ የሚበጅ የጋራ መግባባትን መገንባት ያስፈልጋል ያሉት ፕሮፌሰር አሕመድ፤ በዚህም ሀገራችንን ወደተሻለ የመግባባት ምዕራፍ ለማሸጋገር ጠቃሚ ምክክር እያደረግን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የምክክር ጉባኤ ውጤትም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር የሚበጁ ምክረ ሀሳቦች እንደሚፈልቁበት እምነት እንዳላቸው አንስተዋል።
የካናዳ ዲያስፖራ ማኅበረሰብ ወኪል ተመካካሪና የሕግ ባለሙያ ዳንኤል ወርዶፋ በበኩላቸው፤ የምክክር ባህል የሀሳብ የበላይነትን ለማስረጽ የሚያስችል የጋራ አሸናፊነት መድረክ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የምክክር ጉባኤም በሀገር ውስጥና በውጭ ዓለማት የሚኖሩ ዜጎችን ሁለንተናዊ የተቃና የመግባባት መስተጋብር ለመገንባት መሠረት እየጣለ መሆኑን ገልጸዋል።
ሁሉም የሕዝብ ወኪል አሉኝ የሚሏቸውን ሀሳቦች በማንጸባረቅ የጋራ መፍትሔ፣ መደማመጥ፣ መግባባትና መቀራረብ ባህልን በማጎልበት ሀገርን ያስቀደመ ምክክር እየጎለበተ መምጣቱን ተናግረዋል።
በተመካካሪዎች መካከል እየተፈጠረ ያለው የመግባባት መንፈስም ውስብስብና መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መፍትሔ በመስጠት ሀገርን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር እንደሚያስችል አንስተዋል።
ምክክሩ ችግሮችን ለመካድ ሳይሆን ውስብስብ ችግሮችን አውቆና ቆርጦ በመነሳት ሀገሪቱን ወደ የተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የምክክር ጉባኤው ተመካካሪዎች ያለምንም ገደብና ከልካይ ሀሳባችንን በሙሉ ነጻነት የምናንጸባርቅበት የጋራ መግባቢያ መድረክ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ መምህር ዘላለም ገላው ናቸው።
በሀገሪቱ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም፤ በተመሳሳይ መልኩ ለችግሮቹ የሚሆኑ በርካታ የመፍትሔ ሀሳቦች መኖራቸውን በምክክር ግንዛቤ እንደተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።
በ50፣ በ250 እና በ500 የምክክር ቡድኖች ደረጃ የተካሄደው ምክክርም ችግሩን ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ ለመተንተንና ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልናና የምርጫ ስርዓት፣ በሙስና እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች፣ የሃይማኖት ጉዳዮችና የሰላም ግንባታ አጀንዳዎች ተመካካሪዎች ባቀረቧቸው ምክረ ሃሳቦቻቸው መግባባት ላይ መድረሳቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይፋ አድርጓ።