ቀጥታ፡

ማእከሉ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት እያገዘ ነው

ባህር ዳር ፤ነሀሴ 6/2018 (ኢዜአ)፡ -የባህር ዳር መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት  ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

መንግስት መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎትን በማስፋፋት ዜጎች ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ በዘርፉ የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር እየፈታ ይገኛል።


 

እንዲሁም ዜጎች በአንድ ቦታ የተቀናጀ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ከአላስፈላጊ ወጭና እንግልት ከመታደግ ባለፈ ብልሹ አሰራርን እያስቀረም ይገኛል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ  ኢዜአ ያነጋገራቸው የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የረዳቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አብርሃም ያረጋል እንደገለጹት፣ የባህር ዳር መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ከተማዋን የሚመጥን አግልግሎት እየሰጠ ነው።


 

መንጃ ፈቃድ ለማደስ ወደ ማእከሉ መምጣታቸውን ጠቁመው ቀደም ሲል ከሁለት ቀን በላይ ይወስድ የነበረው እድሳቱ በማእከሉ ከ30 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ አገልግሎቱን ማግኘታቸውን ተናግረዋል ።

የሰራተኞቹም መልካም መስተንግዶ እንዲሁም ግልጽነትና ፍትሃዊነት የሰፈነበት አሰራር አስደሳች መሆኑን ጠቁመው በዚህ ረገድ ብልሹ አሰራር እንዲወገድ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ውባየሁ ጥጋቡ በበኩላቸው የወሳኝ ኩነት መረጃዎችን ለማስፈጸም ከዚህ ቀደም ሁለት ቦታ መሄድ ይጠይቅ እንደነበር አስታውሰው በማእከሉ በሚሰጠው የተቀናጀ አገልግሎት ችግሩ መፈታቱን ተናግረዋል ።

በማእከሉ ምንም አይነት መጉላላት ሳይገጥማቸው ፈጣንና ባጭር ጊዜ ውስጥ የተሳለጠ አገልግሎት ማግኘታቸውን አስረድተዋል።


 

የባህር ዳር መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ማስረሻ ፈንታ በማእከሉ 14 ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በተቋማቱ 91 የተለያዩ አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆኑን አመልክተዋል።

በማእከሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በሚሰጠው አገልግሎት በየቀኑ እስከ 400 የሚደርሱ ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም መፈጠሩን ተናግረዋል።

ማእከሉ ስራ ከጀመረበት ከመስከረም 2018 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ከ75 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተገልጋዮች አገልግሎት መስጠቱ ተመላክቷል ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም