ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር አርአያ የሚሆን ነው

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 6/2018(ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር አርአያ የሚሆን ነው ሲሉ ተመካካሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 . ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪሎች በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።

በምክክር መድረኩ እየተነሱ ያሉት ሐሳቦች ሀገራዊ ሰላምን፣ ዴሞክራሲን እና አብሮነትን ለማጠናከር ጠንካራ መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን ተመካካሪዎች ለኢዜአ ተናግረዋል።

ከተመካካሪዎች መካከል ወጣት ዳንኤል ሲሳይ፣ የሀገራዊ ምክክር የእስካሁን ሂደት በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ እና ትልቅ ሀገራዊ ተስፋ የሚታይበት ነው ብሏል።

ሂደቱ ሀገራዊ የትውልድ ዕጣ ፈንታን በባለቤትነት በመቅረጽ ረገድ ታሪካዊ ፋይዳ እንዳለው በመገንዘብ የሚካሄድ በመሆኑ በተለይም ለመጪው ትውልድ፣ ታዳጊዎች እና ለወጣቶች ብሩህ ተስፋን የፈነጠቀ ነው ብሏል።

አቶ ጸድቻ ሌሌ በበኩላቸው፣ መድረኩ አካታች፣ መከባበር የተሞላበት፣ ሁሉም ሰው በነፃነት ሀሳቡን የሚያንሸራሽርበት እና ጠንካራ ህብረት የታየበት መሆኑን ተናግረዋል።

እያንዳንዱ ተመካካሪ ችግሮችን በምክክር መፍታት እንደሚቻል በማመንም፣ ስሜቱንና ሀሳቡን በግልጽ ያንጸባረቀበት መድረክ መሆኑንም አብራርተዋል።

አቶ ፋራህ ወርሰመ እየተካሄደ ያለው የሀገራዊ ምክክር ሂደት ሁሉንም ያሳተፈ እና የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት ሰፊ ዕድል የሚከፍት መሆኑን ገልጸዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያውያን በምክክር ችግሮቻቸውን ለመፍታት በአንድነት የተሰበሰቡበት ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ በመሆኑ ከጉባኤው የሚጠበቀው ውጤትም አዎንታዊ እንዲሆን ከፍተኛ እምነት እንደሚጣልበት ተናግረዋል።

ይህ አሳታፊ የምክክር ሂደት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ጭምር የገጠሟቸውን ተግዳሮቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደ መልካም ተሞክሮ እና ሞዴል ሊወሰድ የሚችል ነው ብለዋል።

በጉባኤው የተገኙት ገንቢ ውይይቶችና የተደረሱ ስምምነቶችም ለቀጣይ ሰላም፣ ዕድገት እና አብሮነትን ለማጠናከር ታላቅ ምዕራፍ የሚከፍቱ መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም