ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የበጎነት ተግባራዊ መገለጫ ነው- ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን

ሐረር፤ ነሐሴ 6/2018 (ኢዜአ) ፡-የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት በጎነትን በተግባር ለማሳየት ትልቅ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ገለጹ።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ስዩም መኮንን ከሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር ጋር በመሆን በክልሉ የአቅመ ደካማ ዜጎች መኖሪያ ቤት ግንባታን ዛሬ አስጀምረዋል።


 

ከዚህ በተጨማሪ ሚኒስቴሩ ወላጆቻቸው አቅም ለሌላቸው 600 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መስጠት እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም አከናውነዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን በወቅቱ እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ክልሎች በአረንጓዴ አሻራ እና  ሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎችን በማከናወን ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው።

በተያዘው ክረምትም የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎችን በሐረሪ ክልል  ለማከናወን ወደ ስራ መግባቱን  ጠቁመዋል።

በዚህም የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት ግንባታ እንደሚከናወን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ እንዲሁም ወላጆቻቸው አቅም ለሌላቸው 600 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።


 

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራት እርስ በእርስ የመደጋገፍና የሌላውን ችግር የመጋራት እሴትን እያጠናከረና ወንድማማችነትን እያጎለበተ መምጣቱንም ተናግረዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች “በጎነት በተግባር” እየተገለጠበት እንደሚገኝም  ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል።

የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር በበኩላቸው እንዳሉት፤ በክልሉ ከ216ሺህ በላይ  የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የክረምት በጎ ፍቃድ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።


 

በዚህም 47ሺህ ወጣቶች በተለያዩ የልማት ስራዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙና በየዓመቱም ውጤት እየተመዘገበበት እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር በዘንድሮ ክረምት ወደ ክልሉ በመምጣት የሚያከናውነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች  የወገን አለኝታነቱን በተግባር ያሳየ ነውም ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያከናወነው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍም የአቅመ ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎችን ችግር የሚያቃልልና  የመኖሪያ ቤቶቹ ግንባታም ለዜጎች ተስፋን የሚያለመልም እንደሆነ ጠቁመው ለዚህ ተግባርም ምስጋና አቅርበዋል።

በመርሃ ግብሩ የሚኒስቴሩና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የማህበረሰብ ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም