ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስርንና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደትን በማፋጠን ለአፍሪካ የጋራ ብልፅግና ጠንካራ መሠረት እየጣለች ነው - አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስርንና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደትን በማፋጠን ለአፍሪካ የጋራ ብልፅግና ጠንካራ መሠረት እየጣለች ነው - አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስርንና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደትን በማፋጠን ለአፍሪካ የጋራ ብልፅግና ጠንካራ መሠረት እየጣለች መሆኗን በኢትዮጵያ የዛምቢያ አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ ገለጹ።
ዛምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ብዝኅ ዘርፍ የዲፕሎማሲ ትብብር በአዳዲስ መስኮች ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዛምቢያና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የዲፕሎማሲ ወዳጅነት በንግድና የኢንቨስትመንት ትብብር ዘርፍ እየተጠናከረ ነው።
ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስርንና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደትን በማፋጠን በአርአያነት የሚጠቀስና ለአፍሪካ የጋራ ብልፅግና አስደናቂና ጠንካራ መሠረት እየጣለች መሆኗንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናዊ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ በመሠረተ ልማት ትስስር፣ በንግድና ኢንቨስትመንት የትብብር መስኮች የፈጠረችው የልማት አቅም ተምሳሌታዊ መሆኑን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያና ዛምቢያ መካከል የተቋቋመው የጋራ ትብብር ኮሚሽንም ቀጣይ ስብሰባውን በኢትዮጵያ በማካሄድ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያስገኙ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።
ስብሰባውም በሁለቱ ሀገራት መካከል በተለያዩ ዘርፎች እየተካሄዱ ያሉ የትብብር ሥራዎችን ለመገምገምና ወደፊት የሚወሰዱ አዳዲስ የትብብር አቅጣጫዎችን ለመወሰን ወሳኝ እንደሚሆን አመልክተዋል።
በተለይም በንግድ፣ ዲጂታላይዜሽን፣ ሥልጠናና በአቪዬሽን ዘርፍ የትብብር ዕድሎችን በመለየት የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ተጨባጭ የጋራ ጥቅም ለመቀየር የሚያስችል ዕቅድ እየተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዛምቢያና ኢትዮጵያ በምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COMESA) ከሁለቱ ሀገራት ጥቅም ባሻገር የአፍሪካን የጋራ ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረክ ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የኢትዮጵያና ዛምቢያ ግንኙነት ከታሪካዊ የዲፕሎማሲ ትብብር የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያጎለብት ሁለንተናዊ አጋርነት እየተሸጋገረ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የደን መልሶ ማልማትን በማጠናከር ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታና ለዘላቂ ልማት በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኗን አስረድተዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ በደን፣ በውሃና በአካባቢ ጥበቃን የሚያጠናክር የሥነ-ምህዳር ደኅንነት ሚዛንን ለማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የደን ሽፋንን በማሳደግ እያስመዘገበች የምትገኘው የልማት ስኬትም ወሰን ተሻጋሪ ዓለም አቀፍ የልማት ግብ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በትክክለኛ የዕድገት አቅጣጫ እየተንቀሳቀሰች ነው ያሉት አምባሳደር ሙቻንጋ፤ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ግንባታ እመርታዎቿም ለሌሎች የዓለም ሀገራት ጭምር አርአያ ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአህጉራዊ ትስስርና በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች የመሪነት ሚና እየተወጣች መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) እና በምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) በንቃት እየተሳተፈች እንደምትገኝም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ማዕቀፍ የንግድ ልውውጥን ለማቀላጠፍ እየሠራች መሆኑንም አስረድተዋል።