ቀጥታ፡

ፒኤስጂ ከአስቶንቪላ፤ የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ፍልሚያ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2018 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ መርሐ ግብር ዛሬ በፒኤስጂ እና አስቶንቪላ መካከል ይደረጋል።

ጨዋታው ምሽት አራት ሰዓት ላይ ኦስትሪያ በሚገኘው ሬድ ቡል አሬና ይካሄዳል።

የፈረንሳዩ ፒኤስጂ ለዚህ ጨዋታ የበቃው በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ላይ አርሰናልን በመለያ ምት አሸንፎ ዋንጫውን በማንሳቱ ነው።

በሉሲስ ኤነሪኬ የሚመራው ፒኤስጂ ባለፈው የውድድር ዓመትም ላይ ቶተንሃምን በተመሳሳይ በመለያ ምት አሸንፎ የዋንጫው ባለቤት እንደነበር የሚታወስ ነው።

በሌላ በኩል አስቶን ቪላ በአሰልጣኝ ኡናይ ኤምሬ መሪነት በዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ የጀርመኑን ፍራይበርግ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለዛሬው ጨዋታ በቅቷል።

በታሪክ አስቶን ቪላ እ.ኤ.አ በ1982 ባርሴሎናን አሸንፎ ዋንጫውን አንዴ ጊዜ አንስቷል።

ፒኤስጂ እና አስቶን ቪላ ከዚህ ቀደም በአውሮፓ መድረክ የተገናኙት እ.አ.አ 2024/25 የሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ላይ ብቻ ነበር።

በወቅቱ ፒኤስጂ በሜዳው 3 ለ 1 ሲያሸንፍ፥ አስቶን ቪላ በቪላ ፓርክ የ3 ለ 2 ድል አስመዝግቧል። በድምር ውጤት ፒኤስጂ 5 ለ 4 በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ ያለፈ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ መሆን ችሏል።

ይህንን ጨዋታ ይበልጥ ልዩ የሚያደርገው በዳኝነት ረገድ የሚመዘገበው አዲስ ታሪክ ነው።


 

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር (ዩኤፋ) ጨዋታውን በዋና ዳኝነት እንዲመሩ የ34 ዓመቱን ሶማሊያዊ ዳኛ ኦማር አርታንን መርጧል።

ይህም በውድድሩ የ51 ዓመታት ታሪክ ውስጥ የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታን የመሩ የመጀመሪያው የአውሮፓ ዜግነት የሌላቸው ዳኛ ያደርጋቸዋል።

የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የክለቦች ውድድር አሸናፊዎችን የሚያገናኝ የዓመቱ ማጠቃለያና አዲስ የውድድር ዘመን መክፈቻ መርሐ ግብር ነው።

ጨዋታው መደበኛው 90 ደቂቃ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ፥ ወደ ተጨማሪ 30 ደቂቃ ሳይሄድ በቀጥታ ወደ መለያ ምት ያመራል።

የጨዋታው አሸናፊው ቡድን የአምስት ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ሽልማት ሲያገኝ፥ ተሸናፊው ደግሞ አራት ሚሊዮን ዩሮ ወደ ካዝናው ያስገባል።

የውድድሩ ስኬታማ ክለብ ሪያል ማድሪድ ሲሆን ስድስት ጊዜ ዋንጫውን አንስቷል።

ባርሴሎና እና ኤሲ ሚላን በተመሳሳይ በአምስት ዋንጫዎች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም