የኢትዮጵያ ወጣት መልካም ዓላማን አንግቦ የሚንቀሳቀስ የለውጥ ዋነኛ ሞተር ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ወጣት መልካም ዓላማን አንግቦ የሚንቀሳቀስ የለውጥ ዋነኛ ሞተር ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2018(ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ ወጣት መልካም ዓላማን አንግቦ የሚንቀሳቀስ የለውጥ ዋነኛ ሞተርና የሉዓላዊነታችን ጽኑ ማገር ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዓለም አቀፍ ወጣቶች ቀንን በማስመልከት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያን ከወጣቶቿ ነጥሎ ማየት አይቻልም ብለዋል።
የህዝባችን የእድሜ ስብጥር እንደሚያመላክተው ወጣቶች ከፍተኛውን ቁጥር መያዛቸው፣ብልጽግናን ለማረጋገጥና ለማፅናትም ታላቅ እድል ነው ሲሉም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ወጣት መልካም ዓላማን አንግቦ የሚንቀሳቀስ፣ የለውጥ ዋነኛ ሞተርና የሉዓላዊነታችን ጽኑ ማገር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣቱ የሀገሩን ታሪክ በአዲስ ብዕርና ብራና እየጻፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሀገራችንን የኋሊት ጠፍንገው የያዟትን አጓጉል ልማዶች፣ አላስፈላጊ ንትርኮች፣ ጭቅጭቅ እና ግጭቶች በመራቅ የአሁን ወጣት በልማት ላይ አተኩሯል፣ ድህነትን ተጠይፏል ብለዋል።
የመደመር መንግሥት የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና የአመራርነት ሚና ለማጠናከር በትኩረትና በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ሀገራዊ ርዕያችንን ዕውን ለማድረግ ሁላችሁም በንቃት እየተጋን፣ በፍቅር እንድንመላለስ ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።