የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል አቅም ገንብቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል አቅም ገንብቷል
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 5/2018 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አደረጃጀትና አቅም መገንባቱን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለፀ።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ጎብኝተዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ባለፉት አምስት ዓመታት ኮሚሽኑ የተሰጠውን ኃላፊነት እንዲወጣ ላደረገው ድጋፍና ክትትል የምስጋና መርሃ-ግብር ተካሂዷል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ ለውጦችን አስመዝግቧል።
የኮሚሽኑን ሪፖርት ከመገምገም ባለፈም ቋሚ ኮሚቴው የመስክ ምልከታ በማድረግ ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
የአደጋ ስጋት አመራር ፖሊሲን ከመከለስ ባለፈ የአዋጅ ማሻሻያ መደረጉን አንስተው፤ የተለያዩ ደንቦችም ተዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡
ዜጎች ከተረጂነት አስተሳሰብ ተላቀው ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑን በአዳዲስ አሰራሮችና በአዋጅ እንዲደራጅ በማድረግ በኢትዮጵያ ሊደርስ የሚችልን አደጋ አስቀድሞ መከላከልና ሲደርስ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እንዲገነባ ተደርጓል ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ራዕዩን ማሳካት የሚያስችሉ ተስፋ ሰጭ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ራስን በምግብ በመቻል የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት አከናውኗል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ባለፉት አምስት ዓመታት ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
ከለውጡ በኋላ በአዳዲስ አሰራሮችና ህጎችን በማሻሻል ሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን በራስ አቅም ማረጋገጥ የሚያስችል ውጤት አምጥቷል ብለዋል፡፡