ቀጥታ፡

ሀገርን ለመገንባት የሚያስችሉ ሀሳቦች እየመነጩበት የሚገኘው የምክክር ጉባኤ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 5/2018 (ኢዜአ) ፦ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የተሻለች ሀገርን ለመገንባት የሚያስችሉ ሀሳቦች እየመነጩበት መሆኑን ወጣት ተመካካሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣት ተመካካሪዎች እንዳሉት፤ አሁን እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ሂደት በሀገሪቱ የቆዩና ዘላቂ መፍትሔ ያላገኙ መሠረታዊ ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው።

ከመድረኩ የሚወጡ የጋራ ሀሳቦች ለተሻለች ሀገር ግንባታና ለትውልድ መሻገሪያ የሚሆኑ መፍትሔዎችን እንደሚያስገኙም እምነታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሂደቱ ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ ወንድማማችነትና አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት አስታውቀዋል።

ከተመካካሪዎቹ መካከል ወጣት ወንድማገኝ ገርሶ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው ይህ ምክክር ሁሉንም አካላት አሳታፊ ያደረገ መሆኑን ጠቁሟል።

ምክክሩ በሀገሪቱ የነበሩ ግጭቶችን ለማስቀረትና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እጅግ ተገቢና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጿል።

ሂደቱ የሃሳብ የበላይነት የሚከበርበት፣ አንዱ ሌላውን በማከበር ሃሳቡን በነጻነት የሚያቀርብበት መልካም ሁኔታ መፈጠሩን አስታውቋል።

በሂደቱ አማካኝነት ሰላሟ የተረጋገጠ፣ ያደገች፣ የለማችና ሕዝቦቿ በጋራ በፍቅርና በወንድማማችነት የሚኖሩባትን ኢትዮጵያን ማየት እንደሚመኝና እንደሚጠብቅ ተናግሯል።

ሌላኛው ተመካካሪ ወጣት ቢኒያም ትግስቱ በበኩሉ፤ እየተካሄደ ያለው የምክክር ሂደት ሁሉንም አካላት ያካተተና አሳታፊ መሆኑን አንስቷል።

ይህም የነገዋን ኢትዮጵያ በጸና መሠረት ላይ ለመገንባት የሚያስችሉ በጎ ሃሳቦች የተቀኙበት መድረክ እንዲሆን ማድረጉን ጠቅሷል።

ሂደቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተና እያደገ መምጣቱን አንስቶ፤ የተሻገረችና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችሉ ጠቃሚ ሃሳቦች እየመነጩበት እንደሚገኝ ገልጿል።

መድረኩ ማንኛውም ሃሳብ በነጻነት እየተንጸባረቀበት መሆኑን ያነሳው ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ ወጣት አይፈርስም በላይነህ ነው።

የምክክር መድረኩ የነገዋን ጠንካራ ኢትዮጵያ ለመገንባት ትልቅ መፍትሔ ያመጣል ሲል ተናግሯል።

በተጨማሪም ተመካካሪዎች በጋራ የሚደርሱባቸውን ስምምነቶች ሕዝቡም ተቀብሎ ተግባራዊ እንደሚያደርጋቸው ትልቅ ተስፋ እንዳለው ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም