ቀጥታ፡

በድሬዳዋ አስተዳደር የወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከል ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል

 ድሬደዋ፣ ነሃሴ 5/2018(ኢዜአ) ፡-በድሬዳዋ አስተዳደር የወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከል ተግባር በተቀናጀ ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ገለጸ።

የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ አስተዳደሩ የወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከል ተግባር በተቀናጀ ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በዚህም የወባ እና የደንጊ ትኩሳት በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስራዎች በቅንጅት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።


 

በተለይ የወባ ትንኝ መራቢያ በሆኑ ቦታዎች ላይ የፀረ-ትንኝ ኬሚካል ርጭት በማካሄድና ውኃ ያቆሩ ስፍራዎችን በማጽዳት ረገድ ሰፊ የሕብረተሰብ ንቅናቄ ሥራ በመሥራት የአጎበር ስርጭት መካሄዱን ጠቁመዋል።

በወባ በሽታ የሚያዙ ወገኖችም ፈጣን ሕክምና እንዲያገኙ ከመደረጉም በላይ፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎትና በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ስለ በሽታው መከላከል የግንዛቤ ማስጨበጥና የቅኝት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

በአስተዳደር ደረጃ የወጣውን የጽዳት ሕግ በተቀናጀ መንገድ በመተግበር የወባና ተላላፊ በሽታዎችን ከመከላከል ባሻገር፣ ጽዱ ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በገጠርና በከተማ በሚገኙ የጤና ተቋማት ወባን ከመከላከል ባሻገር፣ በተላላፊ በሽታዎች የተያዙ ሰዎችን አክሞ የማዳን ኃላፊነት በላቀ ዝግጁነትና ብቃት እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም