የዘላቂ የሰላም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የድርሻችንን እንወጣለን- የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
የዘላቂ የሰላም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የድርሻችንን እንወጣለን- የሃይማኖት አባቶች
ገንዳ ውኃ፤ ነሐሴ 5/ 2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን የዘላቂ የሰላም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።
ይህ የተገለጸው "የሃይማኖት አባቶች ሚና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ በገንዳ ውሃ ከተማ በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ ነው።
የመድረኩ ተሳታፊ የሆኑት መልዓከ ኤዶም ማህቶት ማንደፍሮ፣ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በሚከናወኑ ተግባራት የሃይማኖት አባቶች የላቀ ሚናችንን በተደራጀ መልኩ መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በዚህም አብሮነትና ወንድማማችነት እንዲጠናከር የማድረግ ስራን አጠናክረን እንቀጥላለን በማለት አክለዋል።
ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን በመገንዘብ፣ ማህበረሰቡ ከተሳሳቱ መረጃዎችና አሉባልታዎች ተጠብቆ፣ በእውነት ላይ የተመሠረተ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ በትብብር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
ሌላኛው ተሳታፊ ሼክ ሙሐመድ አብዱልከሪም በበኩላቸው፣ "ህዝቡ እርስ በእርስ በመከባበርና በመደጋገፍ ለአካባቢው ሰላም መከበር የድርሻውን እንዲወጣ የማስተማርና የማንቃት ኃላፊነታችንን እንወጣለን" ብለዋል።
መምህር ዳኘ አዲስ በበኩላቸው፣ "ለእውነተኛ ሰላም መስፈን በመቻቻል፣ በቅንነትና በወዳጅነት ተባብሮ መኖር ይገባል" በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ህዝቡ የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ ግዴታው እንደሆነ በመገንዘብ፣ የሃይማኖት ትምህርቶች በጥልቀትና በስፋት መስጠታችንን አጠናክረን መቀጠል ይገባናል ሲሉም አስገንዝበዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ ከንቲባ ተወካይ አቶ አዳነ ሀሰን፣ "የሃይማኖት አባቶች ሰላምን ለማስፈንና ማህበራዊ አብሮነትን ለማጠናከር እስካሁን ያደረጉትን በጎና ሚዛናዊ አስተዋጽኦ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል" ብለዋል።
ዘላቂ ሰላምን እውን ማድረግ የሚቻለው ማህበረሰቡን በእውነትና በደግነት መንገድ ላይ በመምራት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሰላምን፣ መቻቻልን እና አብሮነትን በመስበክ ረገድ የእምነት አባቶች እያበረከቱት ያለውን ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ነው ያሉት።
ህዝቡን ከከፋፋይ ንግግሮች፣ ከተሳሳቱ መረጃዎችና አሉባልታዎች በመጠበቅ፣ እውነትንና ፍቅርን መሰረት ያደረገ ግንዛቤ በማህበረሰቡ ዘንድ መፍጠር እንደሚጠበቅባቸውም አብራርተዋል።