የጋራ መግባባትን ለማጠናከር ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የታሪክ ድልድይ - ሀገራዊ ምክክር - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ መግባባትን ለማጠናከር ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የታሪክ ድልድይ - ሀገራዊ ምክክር
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 5/2018 (ኢዜአ) ፦ በመካሄድ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የጋራ መግባባትን ለማጠናከር እና የተሻለች ሀገርን ለመገንባት ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የታሪክ ድልድይ ነው።
የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።
ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ 4 ሺህ የሕዝብ ወኪሎችም በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።
የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በስፋት የተሳተፉበት ይህ መድረክ፤ የዜጎችን ሀሳብ በማቀናጀት የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም፣ አብሮነት እና የጋራ መግባባትን ለማጠናከር ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ወሳኝ ምዕራፍም ነው።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመካካሪዎች እንደሚሉት፤ ምክክሩ የጋራ መግባባትን በማጎልበት ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት ሰፊ ዕድል ከፍቷል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፕሬዝደንት ጽህፈት ቤት ሀላፊ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ የሆነ ታሪካዊ ማካፈያ ስርዓት ነው ብለዋል።
ምክክሩ በኢትዮጵያ ቀደም ሲል መግባባት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ በመምከር ወደ መፍትሄ ለመቅረብ የሚያስችል ትልቅ ስርአት ነው ብለዋል።
ይህ ታላቅ ሁነት ባሳለፍነው የጦርነት ታሪክና አለመግባባትን በምክክር በመፍታት ሰላሟ የተረጋገጠና የልማት ጎዳና ላይ ባለችው ኢትዮጵያ መሃከል ያለ ልዩ የታሪክ ድልድይ ነው ብለዋል።
ምክክሩ ከተለያየ አስተሳሰብ እና የአኗኗር ዘዬ የመጣውን ማህበረሰብ እርስ በእርስ የመተዋወቅ እድልን አስፍቷል ብለዋል።
ሌላኛዋ ተመካካሪ ሜሪ ደስታ በበኩላቸው፤ በምክክሩ ተመካካሪዎች ሀሳባቸውን በነፃነት ለመግለጽ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን ገልጸው፤ የሀሳብ ልዩነቶች ቢኖሩም በሚያግባቡን ጉዳዩች ላይ በማተኮር እየተመካከርን ነው ብለዋል።
ምክክሩ ለትውልዱ አንድነቷ የተጠናከረና የበለጸገች ሀገር የምናሻግርበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ምክክሩ ከአጀንዳ አሰባሰብ ጀምሮ አሁን እስካለበት ሂደት ድረስ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች አካታችና አሳታፊ ያደረገ እንደነበር የገለጹት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ አብርሀም ሀይሌ ናቸው።